ለቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ፡፡
ከቢሮው የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው ቀደም ሲል በተዘጋጀው የከተማዋ መሪ ፕላን 157 በላይ ቅርሶች ተለይተው እንደነበርና ማስተር ፕላኑ በቅርቡ ለ10ኛ ጊዜ ተግባራዊ ሲሆን 400 ያህል ቅርሶች በማስተር ፕላኑ እንዲካተቱና እንዚህን ቅርሶች በመጠበቅና በመንከባከብ ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋጋሩ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትም እየተከናወኑ ነው፡፡
በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉት ዘርፈ ብዙ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችም በእነዚህ ቅርሶች ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ጥንቃቄ እተደረገ ነው፡፡
ለቅርሶች ልማትና እንክብካቤ በተሰጠው ትኩረትም በእንጦጦ 4ሺህ 200 ሄክታር መሬት የሚያለማና ለቱሪስት መስህብ ምቹ የሚያደርግ የፕሮጄክት ጽሕፈት ቤት መቋቋሙን ተገልጿል፡፡
የፕሮጄክቱ ሥትራቴጂክ ፕላንም ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት እንደሆነም ታውቋል፡፡
ቅርሶችን በዓይነት፣ በይዘትና በመጠን በተደራጀ መልኩ የሚገለጽ ዳታ ቤዝ እስከ ወረዳ ድረስ እንደተዘጋጀም ተጠቅሷል፡፡
የአዲስ አበባን አጠቃላይ ገፅታ ቅርሶችን ጨምሮ በ360 ዲግሪ የሚያስተዋውቅ ካርታና ተንቀሳቃሽ ምስል በ17 የመዲናዋ ዋና ዋና ቦታዎች ላይ እንተደተተከሉም መረጃው ያመለክታል፡፡ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያም ለ24 ሰዓት አገለግሎት ሚሰጥ የቱሪስት መረጃ ማዕከል እንደተቋቋመም ታውቋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመትም መዲናዋን ከጎበኙ 200ሺህ 407 ቱሪስቶች 10 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ማግኘት ተችሏል፡፡
በተለይም ባለፉት አስርት ዓመታት ዘርፉ በ10 በመቶ እያደገ እንደሆነና እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 የአውሮፓ የቱሪዝምና ንግድ ምክርቤት ኢትዮጵያን ቁጥር አንድ የቱሪስት መዳረሻ ሀገር አድርጎ እንደመረጣት ይታወሳል፡፡