በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ የተሰየመው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት አካዳሚ በመጪው ማክሰኞ እንደሚመረቅ ክለቡ አስታወቀ፡፡
የክለቡ የሕዝብ ግንኑነት ኃላፊ አቶ ምንሊክ ግርማ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የስፖርት አካዳሚ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
በምረቃው ዕለት የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንደሚገኙ አቶ ምንሊክ አክለው ገልጸዋል፡፡
በመጪው ቅዳሜ መነሻቸውን መስቀል አደባባይ ያደረጉ 20 አውቶቡሶች ደጋፊዎችን በመያዝ ወደቢሾፍቱ ጉዞ እንደሚያደርጉም ታውቋል፡፡
አካዳሚው በቢሾፍቱ ከተማ በ24ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ከ100 በላይ ታዳጊ ስፖርተኞችን ማስተናገድ የሚያስችል አቅም አለው፡፡
አካዳሚው ሁለት የእግር ኳስ ሜዳዎች፣ የምግብ አዳራሽ፣ የመሰብሰቢያ አዳረሽ፣ የመጫዎቻ ክፍሎች፣ መልበሻ ክፍል፣ ዘመናዊ የሕክምና ማዕከል እንዲሁም የጂምናዚየም ማዕከልን ያካከተተ እንደሆነ አቶ ሚኒሊክ አክለው ገልጸዋል፡፡
የግንባታው ወጪ በክለቡ ዳገፊዎችና አጋር ድርጅቶች እንደሸፈነ ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የእግር ኳስ ክለብ የሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ በክለቦች ታሪክም የመጀመሪያውን የወጣቶች የስፖርት አካዳሚ በማስገንባትም ቀዳሚ መሆን ችሏል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ክለብ በ1928 ዓ.ም. እንደተመሰረተ ይታወቃል፡፡
ክለቡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን 13 ጊዜ ያሸነፈ ሲሆን በዘንድሮው የውድድር ዓመትም በመሪነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ዋልታ ኢንፎርሜሽ ማዕከል ዘግቧል፡፡