ከኢትዮጵያ የህዝቦች የኋላ ታሪክ ጋር ተመሳሳይነት ያለውናየሚነገሩ አፈ ታሪኮችን የሚያረጋግጥ ሳይንሳዊ የዘረ መል ግኝት ይፋ ተደረገ ።
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ባዘጋጀው የሳይንስ ውይይት ላይ እንደተገለጸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከለንደን ዩኒቨርስቲ የተውጣጡ ባለሙያዎች ከ 1ሺ100 በላይ የሰዎችን ዘረ መል ናሙና በመውሰድ ያካሄዱት ጥናት ውጤት በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ህዝቦችን የኋላ ታሪክና እንቅስቃሴን ያመላከተ ነው ።
የጥናቱ አስተባባሪ ፕሮፌሰር እንደሻው በቀለ ስለዘረ መል ጥናቱ ባብራሩበት ወቅት እንደገለጹት የኢትዮጵያ ህዝቦች የዘር መል አይነት የዓለም ዘረ መል ሁኔታን የሚወክል ሲሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ግን ከአንድ የዘር ግንድ እንደመነጩ ጥናቱ የሚያረጋገጥ ነው ብለዋል ።
ጥናቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች የዘረ መል አወቃቀርና ታሪክ ምን ይመስላል የሚለውን ላይ ትኩረት በማድረግ የተካሄደ መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰር እንደሻው ባለፉት ዓመታት የነበሩትን የህዝቦች ፍልሰትና ሲነገሩ የነበሩ አፈ ታሪኮችን ትክክል መሆናቸውን ያነጸባረቀ መሆኑን ተናግረዋል ።
እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ እንደዚህ አይነት ጥናቶች የህዝቦችን የዘረ መል የኋላ ታሪክ በመገንዘብ ትክክለኛ ህክምናና መድሓኒትን ጥቅም ላይ ለማዋል ትልቅ እገዛ ይኖራቸዋል ።
ኢትዮጵያ የሰው ዘር የፈለቀባትና በዓለም ላይ የሚገኙ የሰው ዝርያዎች መገኛ በመሆኗን የአሁኑም ጥናት ያረጋጋጠው ጉዳየ መሆኑን ፕሮፌሰሩ አያይዘው ገልጸዋል ።
ዘረ መል ላይ የሚካሄደው ጥናቱ ገና ያላለቀና ለወደፊቱ ተስፋ ሰጪ ግኝቶችን ይፋ ያደርግበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ፕሮፌሰሩ መግለጻቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።