በድርቁ ለተጎዱ አካባቢዎች በቂ የሎጂስቲክ ድጋፍ እየተደረገ ነዉ-ኮሚሽኑ

ብሄራዊ የአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን  በድርቁ ለተጎዱ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚያስፈልገዉ የሎጂስቲክ አቅርቦት  በበቂ ሁኔታ እየቀረበ መሆኑን አመለከተ፡፡

በኮሚሽኑ  የአቅርቦትና ሎጂስቲክስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አይደሩስ ሀሰን ለዋልታ እንደገለፁት በቅድመ ትንበያዉ መሰረት በድርቅ ለተጠቁ አካባቢዎች የሚያስፈልገዉ የሎጂስቲክ ድጋፍ በኮሚሽኑ አማካኝነት እንዲሟላ ከተደረገ በሗላ ለየአካባቢዎቹ በበቂ ሁኔታ እየተሰራጨ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለምግብ 597.9 ሚሊየን ዶላር ፣ ለእናቶችና ህጻናት ለሚሆን አልሚ ምግብ 90 ሚሊየን ዶላር፣ ለግብርና 40 ሚሊየን ዶላር እንዲሁም ለዉሃና ንፅህና 86.5 ሚሊየን ዶላር በአጠቃላይ 921 ሚሊየን ዶላር ያስፈልግ የነበረ ሲሆን ፍላጎቱ ሙሉ በሙሉ ተሟልቷል ማለት ባይቻልም ለተረጂዎቹ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል አቅርቦት መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡

በአገር ደረጃ በ51 ዞኖች በድርቁ ለተጎዱ ሰዎች ድጋፍ የሚያስፈልግ ሲሆን በዚህ አመት 824 የእርዳታ ማሰራጫ ጣቢያዎች ተከፍተዉ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን ይህም አምና ከነበሩት 1092 ጣቢያዎች ጋር ሲነፃፀር የድርቁ ስርጭትና የተፅዕኖ አድማስ መቀነሱን እንደሚያሳይ አስገንዝበዋል፡፡

ባለፈዉ አመት የተከሰተዉን ድርቅ ለመከላከል ከተገዛዉ እህል 59 ሺህ ሜትሪክ ቶን የሚሆነዉ ወደዚህ አመት መሸጋገሩን የገለጹት ዳይሬክተሩ ተጨማሪ ከ185 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ለመጠባበቂያ እንዲሆን ተገዝቶ ከወደብ ይገባል ተብሎ እየተጠበቀ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ከአገሪቱ የመጠባበቂያ እህል ክምችት እንዲሁ ከ141 ሺህ በላይ አቅርቦት በመገኘቱ በአጠቃላይ ወደ 386 ሺህ ሜትሪክ ቶን በአሁኑ ሰአት በኮሚሽኑ እጅ እንደሚገኝና ከዚህም በተጨማሪ ከ14 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ካለፈዉ አመት የተሸጋገረ ሲሆን ከ3 ሜትሪክ ቶን በላይ ተጨማሪ ግዠ በመፈፀም አቅርቦቱ እየተከናወነ መሆኑንም አክለዉ ገልፀዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከ10 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ አልሚ ምግብ እና ከ2900 ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብ ዘይት ለአቅርቦት ዝግጁ መደረጉን አመልክተዋል፡፡

አሁን ካለዉ የእህል መጠን በተጨማሪ ከ26 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ተጨማሪ የእህል ግዥ መፈጸም እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡