በዘንድሮ የበጀት ዓመት ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ከተደረጉት 50 አይነት መድሓኒቶች ውስጥ 8 የሚሆኑት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ መደረጉን የኢትዮጵያ የምግብ ፣ መድሓኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ ።
የባለሥልጣኑ የጤና ተቋማት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ እንዳለ ለዋልታ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ባለፉት 9 ወራት በውጭ ተመርተው ወደ አገር ውስጥ ከገቡት መድሓኒቶች ውስጥ 8 የሚሆኑት በድህረ ገበያ ቅኝት ተገምግመው የአገሪቱን መስፈርት ባለሟሟላታቸው ምክንያት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ተደርጓል ብለዋል ።
ባለሥልጣኑ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መድሓኒቶችን በውጭ አገር የአመራረቱን ሂደት በማየት ፣በመግቢያና በመውጫ ኬላዎች የመቆጣጣር ሥራዎችንበማካሄድ እንዲሁም በገበያ ላይ እያሉ ጥናት በማድረግ የአገሪቱን የመድሓኒት ጥራት ስለሟሟለታቸው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያድረግ አቶ ገዛኸኝ አስረድተዋል ።
መድሓኒቶች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት በሞጆ ደረቅ ወደብ ፣ በአደማና በቃሊቲ ጉምሩክ ጣቢያ ብቻ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ገዛኸኝ በህገወጥ መልኩ የሚገቡትን መድሓኒቶች ለመከላከል በኬላዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል ።
ባለሥልጣኑ የተለያዩ የአገሪቱ ተቋማት ትክክለኛ መድሓኒቶች ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲውሉ ለማድረግ የቁጥጥር ሥራዎች ያካሄዳል ያሉት አቶ ገዛኸኝ በዘንድሮ የበጀት ዓመት 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡና መስፈርት የሟያሟሉ መድሓኒቶች ተገኝተው እርምጃ እንዲወሰድ መደረጉን ገልጸዋል ።
በተለይ የኢትዮጵያ መድሃኒት ፈንድ አቅርቦት አጄንሲ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲውል የሚገዛቸው መድሓኒቶች በአግባቡ ለህብረተሰብ አገልግሎት መዋላቸውን ለማረጋገጥ በሆስፒታሎች ፣ በጤና ጣቢያዎችና ኬላዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል የፋርማሲ ሶፍትዌር ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ ውሏል ።
ኢትዮጵያ በአጠቃላይ 82 በመቶ የሚሆነውን የመድሐኒት ፍላጎቷን የምትሸፍነው ከውጭ በሚገባው የመድሓኒት ምርት ሲሆን ቀሪው 18 በመቶ የሚሆነው በአገር ውስጥ በፋብሪካዎች ምርት የሚሸፈን ነው ።