የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃይል ልማት ቢሮ ውጤት ተኮር አሠራሮችን የሚያጎለብት የአሠልጣኞች ሥልጠና መሥጠት መጀመሩን አስታወቀ ።
የቢሮው የሥልጠናና ጥናት ዳይሬክተር ወይዘሮ ዘበናይ ሸጋና ለዋሚኮ እንደገለጹት ቢሮው 600 ለሚሆኑ የሲቪል ሰርቪስ አመራሮች ለአራት ቀን የሚቆይ የአሠልጣኞች ሥልጠና መሥጠት ተጀምሯል ።
እንደ ወይዘሮ ዘበናይ ሥልጠናው በአራት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩርና ከ88 ተቋማት ለተውጣጡ አመራሮች በሁለት ቦታ የተከፋፈለ ሥለጠና እየተሠጠ ይገኛል ።
የሥልጠናው ተሳታፊዎች በተለያዩ ተቋማት የክፍል ኃላፊዎችና ምክትል ኃላፊዎች መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ዘበናይ በቀጣይ ኃላፊዎቹ በሥልጠናው ያገኙትን ተሞክሮ በሥራቸው ለሚገኙት ሠራተኞች ያካፍላሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል ።
ሥልጠናው በዋናነት በሥራ ጊዜ አጠቃቀም ፣ኃላፊነትን በመወጣት ፣ በካስኬዲንግ ተግባራዊነትና በሥራ አፈጻጻም ግምገማ ርዕሳነ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር መሆኑን አቶ ዘበናይ አብራርተዋል ።
እየተሠጠ የሚገኘው ሥልጠና ዓላማ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛው የሥራ ጊዜውን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያውል ፣ የተገልጋይ እርካታን እንዲያሳድግና የክህሎትና እውቀት ክፍተቱን ለመሙላት እንዲችል መሆኑን አቶ ዘበናይ አስረድተዋል ።
በአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ሰርቪስ አሠልጣኞች ሥልጠና በሚቀጥለው ወር ይጠናቀቃል ተብሎ የሚገመት ሲሆን በአጠቃላይ 3ሺ አመራሮችን ለማሳተፍ ታቅዷል ።