በኦሮሚያ ክልል 3 ሚሊዮን ለሚሆኑ የድርቅ ተጎጂዎች ድጋፍ እየተደረገ ነው

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ለ3 ሚሊዮን የሚጠጉ በድርቅ ተጋላጭ ለሚሆኑ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ድጋፍ እየተሠጠ እንደሚገኝ የኦሮሚያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ ።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ገረመው ሊቃ ለዋሚኮ እንደገለጹት በኦሮሚያ ክልል  ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ ሁኔታ ጥናት ከተደረገ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የድርቅ ተጎጂዎች ከጥር ጀምሮ ድጋፍ ሲደረግ ቆይቷል ።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ 3 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ለምግብ ተረጂነት መዳረጉን የጠቆሙት አቶ ገረመው በተለይ የቦረና ፣ ምዕራብ ጉጂ ፣ባሌ፣ ምዕራብ ሐረርጌ ፣ ምስራቅ ሐረርጌ፣ ምዕራብ አርሲና ምስራቅ አርሲ በድርቁ ክፉኛ የተጎዱ ዞኖች ናቸው ብለዋል ።

የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት የድርቅ ተጠቂ ወገኖች አስፈላጊው እርዳታ እንዲደርሳቸው ጥረት እየተደረገ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ገረመው የክልሉ መንግሥት በየወሩ የምግብ ፣ የመጠጥውሃና የእንስሳት መኖ እርዳታ የሚውል 198 ሚሊዮን ብር እየመደበ መሆኑን አስረድተዋል ።

በተለይ ከፍተኛ  የውሃ እጥረት  ባለባቸው 3 ነጥብ 5  ሚሊዮን የሚሆኑ ዞኖች 200 የሚሆኑ  ቦቴዎች ለሰውና ለእንስሳት  አገልግሎት የሚውል የመጠጥ ውሃ እያከፋፋሉ መሆኑን አቶ ገረመው አያይዘው ገልጸዋል ።

እንደ አቶ ገረመው ገለጻ በኦሮሚያ ክልል በድርቁ ምክንያት የከብቶች መኖ እጥረት ባጋጠማቸው አምስት የሚሆኑ ዞኖች ከጥር ጀምሮ በፌደራል መንግሥት ድጋፍ 702ሺ 998  እሥር  የመኖ ሣር ለማከፋፋል ተሞክሯል ።

በተያዘው የመጋቢት ወርም ክልሉ ከፌደራል መንግሥት ጋር በመተባባር 240ሺ እሥር ሣር  ለቦረና ፣ 60ሺ ሣር ለምዕራብ ጉጂ  ለማከፋፈል ርብርብ እየተካሄደ መሆኑን አቶ ገረመው አመልክተዋል ።

በኦሮሚያ ክልል በድርቅ ያልተጠቁ ወረዳዎች በድርቅ ለተጉዱት ወረዳዎች የምግብ ፣ የውሃና የከብት መኖ ድጋፍ በማድረግና በህብረተሰብ ውስጥ የእርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህሉን በማጎልበት ሰፊ የድርቅ መከላከል ዘመቻ እየተካሄደ ነው ብለዋል አቶ ገረመው ።

በቅርቡ የአማራ ክልል በኦሮሚያ ክልል ድርቅ ተጎጂዎች የሚውል የምግብ እርዳታና የውሃ ቦቴዎች ድጋፍን ያደረገ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን የትግራይ ክልል በዚህ ሳምንት ለኦሮሚያ  ክልል የድርቅ ተጋላጮች የሚውል 150 ኩንታል የከብቶች አልሚ ምግብ ድጋፍ  አድርጓል ።