የአልባሳር ዓለም አቀፍ ፋውንዴሽን ከሚያዚያ 20-ግንቦት 18፣ 2009 ዓ.ም. የዓይን ሕክምና ለመስጠት ዝግጅቶችን እያጠናቀቀ እንደሆነ ገለጸ፡፡
የፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ተወካይ መምህር ያሲን ራጁ ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ሕክምናው የሚሰጠው በጋምቤላ፣ ድሬዳዋ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች ከ40ሺህ ላላነሱ ዜጎች የሕክምና አገልግሎቱን እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡
ለሕክምና የሚያስፈልጉት ወጪዎች የዓይን መነጽርን ጨምሮ ከፋውንዴሽኑ በነፃ እንደሚሰጡም ተገልጿል፡፡
የህክምና ባለሙያዎች ከሱዳን፣ ፓኪስታንና ሳኡዲአረቢያ ተውጣጡና ከሰባት አስከ አስር ዓመት የሥራ ልምድ ያላቸው እንደሆኑ ተመለክቷል፡፡
የዓይን ሕክምናውን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን እንዲቻል የጤና ጥበቃ ሚንስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ የዳያስፖራ ማሕበረሰብና ክልሎች ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነም መምህር ያሲን አክለው ገልጸዋል፡፡
ፋውንዴሽኑ በአፍሪካና በእስያ 27 ሆስፒታሎችን እንዳስገነባና በኢትዮጵያም በመጪዎቹ አስር ዓመታት ውስጥ ስምንት ሆስፒታሎችን ለማስገንባት 1ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በመመደብ እንቅስቃሴ ጀምራል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመትም በአዲስ አበባ 200 ሚሊየን ብር በመመደብ የዓይን ሕክምና መስጫ ማዕከል ለማስገንባት ፋውንዴሽኑ ቅድመ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀ ነው፡፡
ቀደም ሲል ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ ከ125ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የዓይን ሕክምና እንደሰጠና ከ20ሺህ በላይ ለሚሆኑት ደግሞ የዓይን ብርሃናቸውን እንደመለሰላቸው ተገልጿል፡፡
መምህር ያሲን የኢትዮጵያና ሳኡዲአረቢያ ወዳጅነት ከ1ሺህ 400 ዓመት በላይ እንዳስቆጠረ ጠቅሰው፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ወዳጅነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር ከሚደረጉት ተግባራት መካከል የዓይን ሕክምና በጎ አድራጎት ሥራዎች ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡ ሕክምናው የበጎ አድራጎት ሕክምና ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከርና የዕውቀት ሽግግርን ዕውን ለማድረግም እንደሚያግዝ ታውቋል፡፡
በየደቂቃው አንድ ሕጻን የዓይን ብርሃኑን እንደሚያጣ የዓለም ጤና ድርጅትን ጠቅሶ ዋሚኮ ዘግቧል፡፡