በአዲስ አበባ ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ ፕሮጀክቶችን እያካሄደ መሆኑን የአዲስ አበባ የውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን አስታወቀ ።
የባለሥልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እስጢፋኖስ ብስራት ለዋሚኮ እንደገለጹት በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የመጠጥ ውሃ ፍላጎት ለማስተናገድ የአጭርና የመካከለኛ እንዲሁም የረጅም ጊዜ ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ ።
በአዲስ አበባ ከተማ በአሁኑ ወቅት በቀን 608 ሺ ሜትር ኩብ ውሃ ለነዋሪዎች እየቀረበ መሆኑን የጠቆሙት አቶ እስጢፋኖስ የከተማዋን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን ለማሳደግ በቀን 294 ሺ ሜትር ኩብ ውሃ ማምረት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ ነው ።
በአጭር ጊዜ የሚደርሱት ፕሮጀክቶች በአዲስ አበባ ከተማ በሰሜን ፣ በምዕራብ ፣ በሰሜን ምዕራብ ፣ በመሃል አዲስ አበባና በኪስ ቦታዎች ላይ በየዓመቱ 20 የሚደርሱ ጥልቅ ጉድጓዶችን በመቆፈር 20ሺ ሜትር ኩብ ውሃን ወደ ሥርጭት ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን አቶ አስጢፋኖስ ተናግረዋል ።
የኮዬ ፈጬ፣ የኖርዝ አያት ፋንታ፣የለገዳዲ ክፍል ሁለት፣ የሰበታ ተፍኪ ጥልቅ ጉድጓድ ውሃና የገርቢ ግድብ ውሃ ፕሮጀክቶች በመካከለኛ ጊዜ ይደርሳሉ ተብለው የሚጠበቁ መሆናቸውን አቶ አስጢፋኖስ ገልጸዋል ።
በአጠቃላይ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ በተጨማሪ 294 ሺ ሜትር ኩብ ውሃን ወደ ሥርጭት ማስገባት እንደሚቻል አቶ አስጢፋኖስ አያይዘው ገልጸዋል ።
እንደ አቶ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን የውሃ ብክነት ለመቀነስ ባለሥልጣኑ የውሃ ምርትና ሥርጭት ለመቆጣጣር የሚያስችል ማዕከላዊ ሲስተም ለመዘርጋት የሚያስችል ጥናትን አሥጠንቷል ።
በተጨማሪም በከተማዋ ለውሃ ብክነት መንስኤ የሆኑትን 189 ኪሎሜትር የሚረዝም አሮጌ የውሃ መስመሮችን ለመቀየር በዘንድሮ የበጀት ዓመት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል አቶ አስጢፋኖስ ።
ባለሥልጣኑ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ያወጣውን የውሃ ጥራት መስፈርትን ያሟላ የመጠጥ ውሃ በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሠራጭ ለማድረግ የላብራቶሪ ጥራትና አቅም የማሳደግእንቅስቃሴ ተጀምሯል ።