በኢትዮጵያ ታሪክ ታላቅ ስፍራ ያላቸው ሌፍተናል ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዮ ።
በጦር ሃይሎች ሆስፒታል ህክምናቸውን ሲከታተሉ የቆዮት ሌፍተናል ጄኔራል ጃጋማ ትናንት በዘጠኝ ሰዓት ሕይወታቸው ማለፉን ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል ።
የሌፍተናንት ጄኔራል ጃጋማ የቀብር ሥነ ስርዓት በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ዘመድ ወዳጆቻቸው በተገኙበት ዛሬ ይፈጸማል።
የ15 ዓመት ልጅ ሳሉ የፋሽስት ጣሊያን ወረራን በሰሙበት ወቅት ከታላቅ ወንድማቸውና ከአጎታቸው ጋር ሆነው በአርበኝነት ለመታገል ወስነው መዝመታቸው ይታወቃሉ። በወቅቱም በዱር በገደል እየተዘዋወሩ የጣሊያንን ወራሪ ሃይል በጀግንነት ተዋግተዋል።
ከጣሊያን ጋር የነበረው ጦርነት በድል ሲጠናቀቅም አገራቸውን በውትድርና ለማገልገል ወስነው በመግባት እስከ ሌፍተናል ጄኔራል ማዕረግ ደርሰዋል።
በ1913 ዓ.ም ከኬሎ ገሮና ከወይዘሮ ጠላንዱ ኢናቱ የተወለዱት ሌፍተናል ጄኔራል ጃጋማ የአንድ ወንድና አምስት ሴቶች ልጆች አባት ነበሩ። 10 የልጅ ልጆችና ስድስት የልጅ ልጅ ልጆች አሏቸው።
በ2001 ዓ.ም “የበጋው መብረቅ” በሚል ርዕስ በሕይወት ታሪካቸው ላይ ያተኮረ መጽሀፍ ታትሞ አንባቢያን ዘንድ መድረሱ ይታወሳል-(ኢዜአ)።