የሌተናል ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ስርዓተ ቀብር ተፈፀመ

የሌተናል ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ የቀብር ስነ ስርአት በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ተፈፅሟል።

ትናንት  በቀብር ስነ ስርአቱ ላይ የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ እና የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ታላቅ ስፍራ ያላቸው ሌተናል ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ባደረባቸው ህመም ሳቢያ በጦር ሃይሎች ሆስፒታል ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው፥ ከትናንት በስቲያ በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል።

ሌተናል ጄኔራል ጃጋማ በታዳጊነት ዘመናቸው ወራሪውን የፋሽስት ጣሊያን ጦር ለመመከት ከእኩዮቻቸው ጋር አብረው ዘምተዋል።

በወቅቱም ከወራሪው ጦር ጋር ባደረጉት ውጊያ በርካታ ድሎችን መጎናጸፋቸው ይነገራል።

ዳር ድንበራቸውን ለማስከበር የሄዱ ከ3 ሺህ በላይ አርበኞች አለቃና መሪም ነበሩ።

“የበጋው መብረቅ” በሚል መጠሪያ የሚታወቁት ጀኔራል ጃጋማ፥ በአምስት አመቱ የወረራ ወቅት በዱር በገደል የጣሊያንን ወራሪ ሃይል በጀግንነት ተዋግተዋል። 

ከጣሊያን ጋር የነበረው ጦርነት በድል ሲጠናቀቅም እስከ ሌተናል ጄኔራል ማዕረግ ደርሰው ሃገራቸውን በውትድርና አገልግለዋል።

በቀድሞው “ሆለታ የጦር ትምህርት ቤትና” አሜሪካ በመሄድም የጦር ትምህርት ተምረዋል።

በ1913 ዓ.ም በምዕራብ ሸዋ ዞን ጅባትና ሜጫ አውራጃ በደንቢ ዮብዲ ወረዳ ከአቶ ኬሎ ገሮና ከወይዘሮ ጠላንዱ ኢናቱ የተወለዱት ጄኔራል ጃጋማ ባለትዳርና የስድስት ልጆች አባት ነበሩ።

ጄኔራል ጃጋማ “የበጋው መብረቅ” በሚል ርዕስ በሕይወት ታሪካቸው ላይ ያተኮረ መጽሀፍ ታትሞላቸዋል-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።