59ኛው የዓለም ቱሪዝም ጉባኤ በሚቀጥለው ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ቱሪዝም ጉባኤ በሚቀጥለው ሳምንት  በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የባህልና ቱሪዝም  ሚኒስቴር አስታወቀ ።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ መዓዛ ገብረመድህን በትናንትናው ዕለት በሠጡት  መግለጫ  ጉባኤው በአፍሪካ የኮንፍረንስ ቱሪዝምን ከማጠናከር ባለፈ የአህጉሪቱን የቱሪዝም ገጽታና ሃብቶችን ለማስተዋወቅ  ያግዛል ብለዋል ።

እንደ  ወይዘሮ  ማዕዛ  ገለጻ  ጉባኤው ከሚያዚያ 10 እስከ ሚያዚያ 13 ድረስ  በአዲስ  አበባ ከተማ በሸራተን ሆቴል የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ዋና ፀሃፊ በተገኙበትና  200 ተሳታፊዎችን  ባሉበት ይካሄዳል ።  

በጉባኤው ከአፍሪካ አህጉር የቱሪዝም መስክ ልማት ተግዳሮቶችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ትኩረት በመሥጠት ውይይት ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚንስትር ዲኤታዋ ተናግረዋል ።

በተጨማሪም የዓለም አቀፍ የቱሪዝም ዘርፍ እንቅስቃሴ ሌላው በጉባኤው ውይይት የሚደርግበት ጉዳይ እንደሚሆን ይጠበቃል ።

በ59ኛው የዓለም ቱሪዝም ጉባኤ የአባል ሃገራት ሚኒስትሮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የቻይና ቱሪዝም አስተዳደር አመራሮችና አለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ዋልታ ሚዲያ ኮርፖሬት ዘግቧል ።