የኢትዮጵያ መንግሥት የድርቅ አደጋ ላጋጠማቸው የሶማሊያ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ በድርቅ ለተጎዱ የሶማሊያ ዜጎች ሰባት ሺህ ኩንታል ሩዝ ድጋፍ አድርጋለች።
ከዚህም በተጨማሪ አምስት ሺህ ኩንታል ዱቄት፣ 30 ሺህ ጣሳ የዱቄት ወተትና 300 ኩንታል ኃይል ሰጪ ብስኩት ለሶማሊያ ድጋፍ ማድረጓ ነው የገለጸው።
በቅርቡ በሶማሊያ በተከሰተው ድርቅ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሶማሊያዊያን ለከፋ ችግር በመጋለጣቸው የአገሪቱ መንግሥት የድጋፍ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ለሶማሊላንድ አስተዳደርም የአልሚና የኃይል ሰጪ ምግቦች እርዳታ ማድረጓ አይዘነጋም።
ሁለቱ ድጋፎች ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ያላትን ወዳጅነትና የችግር ደራሽነት ያረጋገጠችበት መሆኑ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳንና ከኤርትራ የሚመጡ ስደተኞችን በመቀበልም የመጠለያ እና የማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማቅረብ ላይ መሆኗ ይታወቃል።
ይህም ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገሮች ሕዝቦች ያላትን አክብሮትና ከአገራቱ ጋር ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ለመፍጠር ያላትን ፍላጎት ያመላክታል ነው የተባለው።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ800 ሺህ በላይ የጎረቤት አገራት ስደተኞችን ማስጠለል ችላለች-(ኢዜአ) ።