በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ በምህንድስና ለተመረቁ 900 ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለማሠማራት እየሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን አስታወቀ ።
በባለሥልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስጢፋኖስ ብስራት ለዋሚኮ እንደገለጹት ባለሥልጠኑ በዘንድሮ የበጀት ዓመት በሲቪልና በውሃ ቴክኖሎጂ ተመረቀው ሥራ ያጡ 900 ወጣቶችን በማደራጀት በፍሳሽና በውሃ መሥመር ዝርጋታ ሥራዎች ለማሠማራት እየተንቀሳቀሰ ነው ።
ባለሥልጣኑ በመጀመሪያ ዙር 452 የሚሆኑ ወጣቶችን በ51 ማህበራት እንዲደራጁ በማድረግ የአሥር ቀን ሥልጠና መሥጠቱን የጠቆሙት አቶ አስጢፋኖስ ወጣቶቹ ብድር ተመቻችቶላቸው ወደ ፕሮጀክት ሥራቸው በመግባት ላይ ናቸው ብለዋል ።
ወጣቶቹ ወደ ተግባር ሥራ ሲገቡ የመጀመሪያ ጊዜያቸው በመሆኑ ባለሥልጣኑ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ፣ የማማከር እገዛን እንደሚያደርግላቸው የገለጹት አቶ አስጢፋኖስ በየጊዜውም የሥራ አፈጻጻማቸው ላይ ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስረድተዋል ።
ባለሥልጣኑ በምህንድስና ዘርፍ ለተመረቁና ሥራ ያጡ ወጣቶችን በተለያዩ ፕሮጀክቶቹ ተደራጅተው እንዲሠሩ የማድረግ እንቅስቃሴውን አጠናክሮም እንደሚቀጥል አቶ አስጢፋኖስ አያይዘው ገልጸዋል ።
የአዲስ አበባ ጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ኢንተርፕራይዝ ቢሮ በምህንድስና የተመረቁ ሥራ አጥ ወጣቶችን በመመልመል ፣ አስፈላጊውን ግብዓት በሟሟላት ተደራጅተው እንዲሠሩ የማድረግ ሚናውን ተጫውቷል ።