ህብረተሰቡ ከህገ ወጥ እርድ እራሱን እንዲቆጥብ ድርጅቱ  ጥሪ አቀረበ

ህብረተሰቡ ከትንሳኤ በዓል ጋር በተያያዘ በአካባቢው ከሚፈጸሙ ህገወጥ እርዶች  እንዲቆጥብ    የአዲስ  አበባ  ቄራዎች   ድርጅት  ጥሪ  አቀረበ ።

የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር  አቶ ንብረት በቃ ለዋሚኮ እንደገለጹት  የትንሳኤ በዓል በርካታ እርዶች  የሚከናወኑበት  በዓል መሆኑን ጠቁመው  ህብረተሰቡ  ለጤና  ጠንቅና ለአካባቢ  ብክለት ከሚያጋልጡ  ህገ ወጥ  እርዶች እራሱን እንዲቆጥብ ጠይቀዋል ።

የአዲስ  አበባ ቁራዎች  ድርጅት ለትንሳኤ በዓል  ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የአርድ አገልግሎት  እንዲያገኝ ከመቼውም በላይ  ዝግጅቱን  ማጠናቀቁንም  አቶ ንብረት ገልጸዋል ።

ድርጅቱ  በዘንድሮ  የትንሳኤ በዓል ከዋዜማው አንስቶ ከ 3ሺ በላይ የዳልጋ ከብቶችንና  ከ2ሺ በላይ በግና ፍየሎችን ለማረድ ከወዲሁ የእርድ ማሽኖችና ክፍሎች ዝግጁ በማድረግ  ለአገልገሎት  እየተጠባበቀ  ይገኛል ብለዋል አቶ ንብረት ።

ድርጅቱ  ተደራሽነቱን  ለማስፋት  በአቃቂ  በከፈተው ቅርንጫፉን  በማስፋፋት ለትንሳኤ በዓል  በግና ፍየል  የማረድ አቅሙን  450  እንዲሁም   የዳልጋ ከብቶችን የማርድ አቅም 450 ማድረሱን  ተናግረዋል ።

ድርጅቱ በዘንድሮ የትንሳኤ በዓል 1ሺ500 የሚሆኑ በጎችን በማረድ  የህብረተሰቡን አቅም ባገናዘበ መልኩ  የበግ  ሥጋ በሽያጭ መልኩ  ማቅረቡንም አቶ ንብረት አያይዘው  ገልጸዋል ።

የአዲስ አበባ ቁራዎች ድርጅት ለአንድ በግ ወይም ፍየል እርድ በ68  ብር  ለዳልጋ ከብት ደግሞ በ360 ብር ብቻ  ክፍያ  አገልግሎት  ለመሥጠት ተዘጋጅቷል ።