“በዘውዲቱ ሆስፒታል በህክምና ስህተት የወንድማችን ዓይንና ጀሮ ተጎድቶብናል!” -የታካሚ ቤተሰብ

“በዘውዲቱ ሆስፒታል ህክምና በተፈፀመብን የህክምና ስህተት ወንድማችን በአሁኑ ጊዜ ሁለት አይኑ አያይም ፤ሁለት ጆሮዎቹ አይሰሙም”  የታካሚ ቤተሰብ

ታካሚውን ያስተናገዱት ዶክተር በበኩላቸው  “ችግሩ  በህክምና ሂደት የተፈጠረ እንጂ በህክምና ስህተት ወይም ኃላፊነታችንን ባለመወጣታችን የደረሰ አይደለም” ብለዋል ፡፡

“በአስም ህመም ምክንያት ሆስፒታል አስገብተነው 3 ወራት የፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ካቆዩት በህዋላ በተፈፀመብን የህክምና ስህተት ወንድማችን በአሁኑ ጊዜ ሁለት አይኑ አያይም ፤ሁለት ጆሮዎቹ አይሰሙም፤ አይነምድርና ሽንቱን መቆጣጠር አይችልም የሰውነት ከፍሎቹም አገልግሎት አቁመዋል”  ይላሉ የታካሚው ወንድም፡፡

ወደ ዋልታ የመጣ ቅሬታ የዘውዲቱ ሆሰፒታልና ወንድማቸው በዚያው ሆስፒታል ሲታከም ቆይቶ ተፈፅሞብናል ባሉት የህክምና ቸልተኝነት ምክንያት ወንድሜ በሞትና ህይወት መካከል ይገኛል ባሉ ግለሰብ መካከል ውዝግብ ተነስቷል ፡፡

በተጨማሪም አንዳንድ ህክምናዎች እኛ ሳንፈርም ነው የተከናወኑት ያሉት የታካሚው ወንድም ሆስፒታሉ በወንድማችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶብናል ሲሉ ምሬታቸውን ይገልጻሉ ፡፡

በአስም ህመም ወደ ሆስፒታሉ የወሰድኩት ወንድሜ ለዚህ ችግር በመዳረጉ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ቤተሰቦቹ ገብተናል ነው ያሉት

ጉዳዩን የሚመለከተው የመንግስት አካል ያአጣርቶ እርምጃ እንዲወስድላቸውም ጠይቀዋል

በአሁኑ ጊዜም ያለ ኦክስጂን ድጋፍ ለደቂቃ በህይወት መኖር የማይችለው ወንድሜን ከሆስፒታሉ ይዛችሁ ውጡ ተብለናል ከዚህም በላይ ከፍተኛ ማዋከብ እየደረሰብን ነው ሲሊም አመልክተዋል ፤ የታካሚው ወንድም፡፡

ህክምናውን ያደረጉት ዶክተር አደፍርስ ባህሩ “ታካሚው በህክምናው መካከል የልብ ምታቸው በመቆሙ ይህን ለመመለስ ልባቸውን በመጫን የልብ ምታቸውን መመለስ የሚያስችል ህክምና ስናደርግ ቆየተናል” ነው ያሉት

“ይሁን እንጅ በተደረገው ጥረት ለጥቂት ሰከንዶች በአእምሮዋቸውና ልባቸው መካከል ደም መተላለፍ ባለመቻሉ አእምሮዋቸው  ስራውን አቁሟል” ሲሉም ያብራራሉ ፡፡

“በዚህ ምክንያት ታካሚው ዓይናቸው ወዳለማየት ጆሯቸውም አይሰማም ሙሉ በሙሉ ሰውንታቸውን ማዘዝም የማይችሉበት ሁኔታ ተከስቷል” በማለት ነው የገለጹት ፡፡

ግለሰቡም በአሁኑ ጊዜ በኦክሲጂን ድጋፍ በመተንፈስ በሞትና ህይወት መካከል ሲሆኑ ኦክሲጅኑ ከተነቀለ ህይወታቸው እንደሚያልፍ  ያረጋገጡት ዶክተር አደፍርስ፤ “ይህ በሂደቱ የተፈጠረ እንጂ በህክምና ስህተት ወይም ኃላፊነታችንን ባለመወጣታችን የደረሰ አይደለም” ብለዋል ፡፡

የዘውዲቱ  ሆስፒታል  ሜዲካል  ዳይሬክተር ዶከተር አይናለም አየለ በበኩላቸው ከተነሳው ቅሬታ ጋር ተያይዞ  ማጣራት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

ዳይሬክተሩም የህክምና ሂደቱ ስርአቱን ጠብቆ መከናወኑን ገልጠው፤ በህክምና ሂደቱ የታካሚው ጤና አሁን ደረሰበት የተባለው ደረጃ መድረሱን ነው ያስታወቁት ፡፡

አያይዘውም “በህክምና ሂደቱ የታካሚውን አስታማሚ ሳያስፈርሙ የተከናወነ ስራ አለ የተባለውን ጉዳይ እያጣራን ነው” ማለታቸውን ዋልታ ሚድያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት ዘግቧል  ፡፡

አርታዒ – በሪሁ ሽፈራው