የትምህርት ተቋማትን ከአልባሌና አዋኪ ጉዳዮች ነፃ ማድረግ የሚያስችል አስገዳጅ ህግ ለማውጣት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጁመሩን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አስታወቁ ፡፡
የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የስነ-ምግባር ትምህርት አሰጣጥና ውጤትን አስመልክቶ ያቀረበው ጥናት በትምህርት ተቋማት አካባቢ አልባሌና አዋኪ ጉዳዮች ተስፋፍተዋል ብሏል።
የማጠቃለያ አስተያየት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም የትምህርት ተቋማት ከአልባሌና አዋኪ ጉዳዮች ነፃ ለማድረግ አስገዳጅ ህግ ያስፈልጋል የሚለውን ምክረ ሃሳብ ደግፈውታል።
የችግሩ አሳሳቢነት በተደጋጋሚ ቢነገርም ሊፈታ አልቻለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን ለማስወገድ ህግ ማውጣት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀዋል።
ይህም አስገዳጅ ህግ ማውጣት የሚያስችል እንቅስቃሴ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የጥናቱ ምክረ ሃሳብ የተማሪዎችን ተጋላጭነት የሚቀንስ ነው ሲሉ ደግፈውታል።
በትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካባቢዎች የጫት፣ የሺሻና ሃሺሽ፣ የመጠጥ፣ የጭፈራና የቁማር ቤቶች እየተስፋፉ መሆኑንም ጥናቱ አረጋግጧል።
እነዚህ አልባሌና አዋኪ ጉዳዮች የተማሪዎችን ዓላማ በማሳት በአገሪቷ ላይ ትልቅ ኪሳራ እያደረሱ ነውም ብሏል።
የማዕከሉ የመልካም አስተዳደርና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ተመራማሪ አቶ ሄኖክ ስዩም በጥናቱ የቀረበውን ምክረ ሃሳብ አብራርተዋል።
የጥናቱ ምክረ ሃሳብ የትምህርት ተቋማት ቅጥር ግቢዎችን ፅዱና ውብ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ያሟሉና የመማር ማስተማር ሂደቱን ከሚያውኩ ጉዳዮች ነፃ ለማድረግ ጊዜ ሊሰጥ ይገባል ይላል።
ለሱስ ተገዢ መሆን ስለሚያስከትለው ጉዳትና መከላከያው ለተማሪዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ ተገቢ መሆኑንም አሳስቧል ጥናቱ።
በጥናቱ ላይ በተካሄደው ውይይት አስገዳጅ ህግ መውጣት አለበት የሚለው ሃሳብ መግባባት ላይ ተደርሶበታል -(ኢዜአ) ።