አዲስ አበባ ከቀላል ባቡሮቿ መካከል አንዱን በጀርመኗ ላይፕዚች ከተማ ሰየመች

ዛሬ በመዲናዋ በተካሄደ ፕሮግራም የስያሜ የምስክር ወረቀት ለእህት ከተማዋ ላይፕዚች ከንቲባ ተበርክቷል።

ከንቲባ ድሪባ ኩማ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ስያሜው የእህትማማች ከተሞቹን ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክረዋል።

በጀርመኗ ላይፕዚች ከተማ በአዲስ አበባ የተሰየመ የህዝብ ማመላለሻ ባቡር፣ አደባባይና የገበያ ማዕከል መኖሩን ጠቅሰው ይህም በሁለቱ ከተሞች ብሎም አገራት መካከል ያለውን ግንኙነትና ትብብር እንደሚያጠናክረውም ተናግረዋል።

ወዳጅነቱ የአገራቱን ሕዝቦች ተጠቃሚነት ወደሚያረጋግጡ ተግባራት ለመመንዘር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ነው ያሉት።

ስያሜው የከተሞቹን ወዳጅነት ለማጠናከር የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን የተጋሩት የላይፕዚች ከተማ ከንቲባ ቡርካሃርድ ጁንግ በሶስት ዓመታት የተገነባውን የከተማ ቀላል ባቡር አድንቀዋል።

ባቡርና መሰል ዘመናዊ የብዙሃን ማመላለሻ ትራንስፖርት ለከተማዋ ነዋሪዎች ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር ለአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እድገት የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ነው ከንቲባው የተናገሩት ።

ሁለቱ ከተሞች በጋራ በያዙት 'ሁሉን አቀፍ' ፕሮጀክት በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በአካል ጉዳተኞች መብትና በባህልና ኪነ-ጥበብ መስክ የተሰሩ ስራዎችን የጠቀሱት ከንቲባው ትብብራቸው በሁሉም መስክ እንዲሆን እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

አዲስ አበባና ላይፕዚች የእህትማማችነት ስምምነት የተፈራረሙት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2004 ዓ.ም ነው-(ኢዜአ) ።