በኢትዮጵያ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት የሁሉንም ባለድራሻ አካላት ተሳትፎ እንደሚጠይቅ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።
’’ወባን በጋራ ጨርስን እናስወግድ’’ በሚል መሪ ቃል 10ኛው ሀገር አቀፍ የዓለም የወባ ቀን በጋምቤላ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ትናንት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ተወካይ ዶክተር እሸቱ ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ሁሉም አካላት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
ባለፉት ዓመታት የወባ በሽታ የልማት ችግር ከማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በተከናወኑ ሥራዎች በተፈለገው ደረጃ ግቡን ማሳካት መቻሉን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅትም በሽታው የልማት ችግር ከማይሆንበት ደረጃ ማድረስ ብቻ ሳይሆን በፈረንጆች አቆጣጠር 2030 ከሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት እቅድ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚሁ እቅድ መሳካት ከአጋር ድርጅቶች በተጨማሪ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጋትሉዋክ ቱት በዚሁ ጊዜ እንዳስገነዘቡት በክልሉ ባለፉት ዓመታት የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተሰሩት ስራዎች የበሽታውን ስርጭት በእጅጉ መቀነስ ተችሏል።
በቀጣይም የተገኙትን ውጤቶች አጠናክሮ በማስቀጠል በሽታውን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡና የሌሎች ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ እንደሚያሰፈልግ ነው ያመለከቱት።
በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ ተወካይ ዶክተር ኢስተር ሜሪ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የወባ በሽታን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ሥራዎች ማከናወኗን አስረድተዋል።
"በአሁኑ ወቅትም ሀገሪቱ በ2030 የወባ በሽታን ለማጥፋት እቅድ ነድፋ ወደ ሥራ በመግባት ረገድ እያሳየችው ያለው ቁርጠኛነት በእጅጉ የሚደነቅ ነው" ብለዋል።
"ሀገሪቱ ለነደፈችው እቅድ መሳካትም የዓለም የጤና ድርጅት ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል" ያሉት ዶክተር ኢስታር ኢትዮጵያ ግቡን ከሚያሳኩ ሀገራት አንዷ እንደምትሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።
በዓሉ በአውደ ጥናት፣በስፖርታዊ ትርኢት፣በመስክ ጉብኝትና አመራሮች የተሳተፉበት የወባ ምርመራ በማድረግ የተከበረ ሲሆን የፌዴራልና የሁሉም ክልሎች እንዲሁም የዓለም የጤና ድርጅት ተወካዮች ተካፋይ ሆነውበታል-( ኢዜአ) ።