ሁሉንም ወረዳዎች የጤና መድን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ቢሮዉ አስታወቀ

በአማራ ክልል በሁሉም ወረዳዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ፍትሃዊና ቀጣይነት ያለው የጤና መድን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ገለፀ ፡፡ 
የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ብዙአየሁ ጋሻው  እንደገለፁት የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ህብረተሰብ የሚደርስበትንና ህብረተሰቡን ከድንገተኛ ወጭ ለመታደግ የሚያስችለውን ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን በሁሉም ወረዳዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍትሃዊና ቀጣይነት ያለው የጤና መድን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል ፡፡

እንደ አቶ ብዙአየሁ ገለፃ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ህብረተሰቡ በህክምና ወቅት የሚያጋጥመውን ከፍተኛ የገንዘብ ጫና በማስቀረት የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ እና የጤና ተቋማትን የአገልግሎት ጥራት ለማሻሻል የሚያግዝ ስርዓት በመሆኑ ህብረተሰቡ የኢኮኖሚ አቅም ሳይገድበው እንደ ህመሙ ሁኔታ መታከም እንዲችል ያግዛል፡፡

አቶ ብዙአየሁ  ቀደም ሲል በክልሉ 120 ወረዳዎች የማህበረሰብ ጤና መድን አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ መሆኑን ገልፀው በተያዘው የበጀት ዓመት ግን ተጨማሪ 40 ወረዳዎች በአገልግሎቱ እንዲታቀፉ በማድረግ የማህበረሰብ ጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ ወረዳዎችን 160 በማድረስ 3 ሚልዮን አባወራዎችን በማቀፍ ለ15 ሚልዮን የክልሉ ነዋሪዎች ዋስትና የሚሰጥበት አግባብ ይፈጠራል ብለዋል ፡፡

በመሆኑም የማህበረሰብ ጤና መድን አገልግሎት የአንድ ተቋም ብቻ ተግባር ባለመሆኑ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ አመራሮች ጉዳዩን በባለቤትነት ይዘው ሊመሩት እንደሚገባ አሳስበዋል ፡፡