በመኖሪያ አካባቢያችን የተሰበሰበ ቆሻሻ ለረጅም ጊዜ በመቆየቱ ለህመም ተጋልጠናል አሉ

በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳ 2 ነዋሪዎች በመኖሪያ አካባቢያቸው የተሰበሰበ ቆሻሻ ለረጅም ጊዜ በመቆየቱ ለህመም ተጋልጠናል አሉ ፡፡

ቆሻሻውን ተከትሎ ባለቤት አልባ ውሾች በመራባታቸው የአካባቢው ህብረተሰብ በመንከስ ለተጨማሪ በሽታ እንዲዳረግ አድርጎታልም ስጋት ፈጥረብናል ብለዋል፡፡

ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ብናሳውቅም ሰሚ አጥተናል ሲሉ ለዋልታ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በበኩሉ የህብረተሰብ ቅሬታዎችን ሊያስቀሩ የሚችሉ ስራዎችን እየሰራሁ ነው ፣በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ አልቀው አገልግሎት የሚሰጡ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሼዶችን ለማሰራት እንቅስቃሴዎችን ጀምሬያለሁ ብሏል፡፡

የነዋሪዎቹ ቅሬታ ተገቢ እና ትክክል እንደሆነ የጠቀሰው ኤጀንሲው ለችግሩ ጊዚያዊ መፍትሄዎች ለመስጠትም ደረቅ እና የሚበሰብስ ቆሻሻን በመለየት በቴክኖሎጂ የታገዙ ሽታ ማጥፍያ ኬሚካሎችን በመረጨት እንደሚሰራ አስታወቋል፡፡

በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት 74 የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሼዶች በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል በዚህም በተደጋጋሚ የሚነሱ የህበረተሰብ ቅሬታዎችም እንደሚፈቱ ተጠቁሟል፡፡