በሁለት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ከጥር 26 ጀምሮ የጥገና ሥራ ይጀመራል

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከጥር 26 ቀን  2010 ጀምሮ በቤተ ጎለጎታና ቤተሚካኤል የላሊበላ  አብያተ ክርስቲያናት ላይ የጥገና ሥራ ለማከናወን  ዝግጅቶችን ማጠናቀቁን  አስታወቀ ።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ባለሥልጣኑ ከሁለት ቀናት በኋላ በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ በላሊበላ የቤተ ጎለጎታና ቤተ ሚካኤል ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ የጥገና ሥራ ፕሮጀክት  ማከናወን  ይጀምራል።

 

በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ላይ የሚከናወነውን የጥገና ሥራ  ወርልድ ሞኒመንት ፈንድና በአሜሪካ  አምባሳደር ፈንድ እንዲሁም በባለሥልጣኑና  በዩኔስኮ ትብብር  በስድስት ወራት ውስጥ የሚከናወን መሆኑን አቶ ዮናስ በመግለጫቸው  አመልክተዋል ።

ባለሥልጣኑ በላሊበላ የቤተሩፋኤል እና ቤተገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት ላይ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያከናውን የቆየው  የጥገና ሙከራ ፕሮጀክት አስተማማኝና ስኬታማ በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡

በቀጣይ በቤተ ጎለጎታና ቤተ ሚካኤል አብያተ ክርስቲያናት ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ መወሰኑንም በመግለጫው ተጠቅሷል  ።

እንደ አቶ ዮናስ ገለጻ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመታደግ ሜምብሬን በተባለ አዲስ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ጥገናው የሚከናወን መሆኑን ቴክኖሎጂው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ  በቅርሱ ውስጥ  አየር እንዲንሸራሸር የሚያደርግ ነገር ግን  ውሃ የማያስገባ በመሆኑ  የተሻለ ያደረገዋል ብለዋል ።