ሁለተኛው ዙር የጥሩነሽ ቤጅንግ ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቀቀ

ሁለተኛው ዙር የጥሩነሽ ቤጂንግ የኢትዮ-ቻይና ወዳጅነት ሆስፒታል የማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቆ ርክክብ ተፈጸመ።

በቻይና መንግስት ድጋፍ የተካሄደው የማስፋፊያ ግንባታ 25 ሚሊዮን 500 ሺህ የቻይና ዩዋን ወጪ ተደርጎበታል።

የማስፋፊያ ግንባታው በኢትዮጵያ ያለውን የጤና ተደራሽነት ለማስፋትና አገልግሎት አሰጣጡን የተሻለ ለማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋልም ተብሏል።

በርክክብ ስነስርዓቱ የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚንስትር ዴኤታ አቶ ብርሃኑ ፈይሳ እንደተናገሩት “በኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለማሳደግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው”።

ለአብነትም የጤና ተቋማትን መገንባትና በሙያው የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለዚህ እንቅስቃሴ አንድ ምእራፍ የሚከፍተው የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፕታል የማስፋፊያ ግንባታ  ማሳያ መሆኑንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት።

የሁለተኛው ምዕራፍ ማስፋፊያው በሆስፒታሉ የሚሰጠውን የአገልግሎት ተደራሽነት ከማስፋት ባለፈ በሆስፒታሉ ለመገልገል የሚመጣውን የታካሚዎችን መጉላላትን ይቀንሳል ብለዋል።

በመጀመሪያ ዙር በተካሄደው ግንባታ ሆስፒታሉ መቶ የታካሚ አልጋዎች ብቻ ያሉትና የባለሙያዎች ማረፊያ፤ የህሙማን ምግብ ማዘጋጃና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ የቢሮ ጥበቶች እነደነበሩም አንስተዋል።

እነዚህን ችግሮች ለማቃለል የተደረገው ሁለተኛው ዙር የማስፋፊያ ግንባታ በአሁኑ ጊዜ ሁለት መቶ ህሙማንን በአንዴ ማስተናገድ ያስችላል ብለዋል።

በተጨማሪም ሆስፒታሉ  በአዲስ አበባና ኦሮሚያ መካከል የተገነባ በመሆኑ ሁለቱንም አካባቢዎች የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጃን በበኩላቸው ኢትዮጵያና ቻይና  በጤናው ዘርፍ በርካታ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያሳየች ያለው ለውጥ አበረታች መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ ቻይናም ኢትዮጵያን በጤናው ዘርፍ ለመደገፍ እየሰራችና በርካታ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ከዚህም መካከል የሁለቱ አገራት የወዳጅነት ሆስፒታል አየተባለ የሚጠራው የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል በሁለት ዙር ግንባታ አጠናቃ ለተገልጋዮች ክፍት መደረጉን ጠቁመዋል።

አምባሳደር ታን አክለውም በቀጣይም ቻይና በጤናው ዘርፍ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ አንደምትቀጥልና የጤና ባለሙያዎችን በማስመጣት በቻይናና በኢትዮጵያ መካከል  የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ለማድረግ እንደሚትሰራ ገልጸዋል።

የመጀመሪያ ዙር የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል በቻይና መንግስት ድጋፍ እንደ እኤአ በ2012 መገንባቱ ይታወሳል።(ኢዜአ)