በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን አባቶች መካከል የቆየውን አለመግባባት ለመፍታት እንቅስቃሴ ተጀመረ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል የቆየውን አለመግባባት ለመፍታት የእርቅና ሰላም ጥረት ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ።

በውጭ ሀገር በተለይም አሜሪካ በሚገኙትና በአሁኑ ወቅት ሲኖዶሱን በሚመሩት የቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል የተፈጠረው ውዝግብና አለመግባባት ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ  አስቆጥሯል።

4ኛው የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ 1984 . መንበራቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ የተወሰኑ አባቶችን አስከትለው ከሀገር ከወጡ በኋላ ነበር መቃቃሩ የተጀመረው።

ቅዱስ ሲኖዶሱ ይህንን ግንኙነት ሰላማዊ ለማድረግና ምእመኑን በጋራ ማገልገል በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ የጀመረውን የሰላም ጥረት አስመልክቶ ትናንት መግለጫ ሰጥቷል።

የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማትያስ  በዚሁ ወቅት እንዳሉት ከመጪው ሐምሌ 11 ቀን 2010 .  ጀምሮ በከፍተኛ የቤተክርስቲያኗ መንፈሳዊ አባቶች መካከል የቆየውን መቃቃር በማስወገድ እርቅ ለማውረድ የሚያስችል እንቅስቃሴ ይጀመራል።

በዚህም መሰረት በውጭ የሚገኙ አባቶች ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻች የሚደረግ ሲሆን የቤተክርስቲያኗን  አንድነት ወደ ነበረበት ደረጃ አንዲቀዳጅ የሚያስችሉ ተግባራትም ይከናወናሉ ተብሏል።

ቤትክርስቲያኗ በተለያዩ ዘመናት የተፈራረቁባትን የውጭና የውስጥ ፈተናዎች በመቋቋም እምነቷን፣ ቀኖናዋንና ትውፊቷን አፅንታ መቆየቷን ያወሱት ፓትሪያርኩ፤  በቤተክርስቲያኗ የጠፋውን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ ላለፉት ዓመታትም ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ቅዱስ ሲኖዶሱ በዓመት ሁለት ጊዜያት በሚያደርጋቸው ጉባኤዎች የሰላሙ በር ክፍት መሆኑን በመግለጽ የሰላም ጥሪ ሲያስተላልፍ ቆይቷል።

ይህ የምዕመናን ልጆቻቸውን የሰላም ጥማትና የዘወትር ጸሎት የቅዱስ ሲኖዶስ የዕለት ከዕለት የሰላም ጥረት ቅድመ እግዚአብሔረ ደርሶ ሰላማዊ  መቋጫ ወደሚያገኝበት ደረጃ እንዲደርስ 2010 የጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን ተከትሎ በራሱ ተነሳሽነት ከካሕናትና ምእመናን የተውጣጣ የሰላም ኮሚቴ ተዋቅሯል”  ሲሉም ፓትርያርኩ ገልፀዋል።

ኮሚቴው ያቀረበውን የዕርቀ ሰላም ጥያቄ በአዎንታ ተቀብሎ ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው የዕርቅ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ ሦስት ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳትን መሰየሙንም አስታውቀዋል።

በዚሁ መሰረትም ከሐምሌ 11 ቀን 2010 . ጀምሮ በአባቶች መካከል የሚካሄደው የዕርቀ ሰላም ሂደት ፍጻሜ የሚያገኝበት እንዲሆንም አስፈላጊው ጥረት እንደሚደረግ አመልክተዋል።

ይህ ጥረት የሰመረ እንዲሆን መላው የቤተክርስቲያኗ ገዳማትና አድባራት ካሕናትና ምእመናን በጸሎት እንዲተጉም ቅዱስ ሲኖዶሱ አሳስቧል።

በመጨረሻም አሁን በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል የተጀመረው እርቀ ሰላም ያለምንም መሰናከል ለውጤት ይበቃ ዘንድ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ፈቃድ ከተሰጠው አካል በስተቀር ማንም መግለጫ መስጠት እንደማይገባውም አሳስበዋል።(ኢዜአ)