ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተወጣጡ መምህራን ጋር ተወያዩ

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተወጣጡ መምህራን ጋር ተወያይተዋል፡፡

ከ50 ዩኒቨርሲቲዎች ከተወጣጡ 3 ሺህ 175 ከሚሆኑ መምህራን ጋር በጽህፈት ቤታቸው ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ወቅትም ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች የትምህርት ጥራት፣ ሀገራዊ አንድነት፣ የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ፣ ብልሹ አሰራር እና ሙስና፣ የትምህርት ፖሊሲ፣ ብቃት እና ስነምግባር ያለው ዜጋ ስለማፍራት እና ስለ ጥናትና ምርምር ዙሪያ አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ከተሳታፊዎቹ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌጤ ከዚህ ቀደም ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባረው የነበሩት 42 መምህራን ይቅርታ ተደርጎላቸው ወደ ስራቸው እንዲመለሱ በጠየቁት መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ ጠይቀናቸው ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ወስነዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በትምህርት ተቋማተ ውስጥ ያሉ ብልሹ አሰራሮች እና በፖለቲካ አመለካከት እና በሌሎች ሰበቦች የሚደረጉ አድልኦዎች እንደሚስተካከሉም ቃል ገብተዋል፡፡

መንግሰት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በከፍተኛ ተነሳሽነት እየሰራ እንደሆነ እና ወደፊትም ይሄው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡