የተባበሩት አረብ ኢሚሬተስ ለተፈናቃዮች መጠለያ ልትገነባ ነው

 የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ የቀይ ጨረቃ ማኅበር በኢትዮጵያ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል መጠለያ ለመገንባት ከመንግሥት ጋር የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረመ።

የመግባቢያ ሥምምነቱን በማኅበሩ የአደጋ ዝግጁነትና ምላሽ ክፍል ኃላፊ ሳዳ ሞሃመድና የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳመና ዳሮታ ፈርመውታል።

የሚገነባው መጠለያ ከጉጂ፣ ከባሌና ከቦረና ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል ሲሆን፤ በሦስት ምዕራፍ ግንባታ 50 ሚሊዮን ብር ወጪ ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳመና ዳሮታ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የተባበሩት አረብ ኢሚሬተስ ቀደም ሲል ለእነዚሁ ተፈናቃዮች የስንዴና ዘይት ድጋፍ አድርገዋል።

የተደረገው ድጋፍም ወቅታዊና በተለይም ተፈናቃዮቹ ያጋጥማቸው የነበረውን የምግብ እጥረት ለማቃለል ሚናው ከፍተኛ እንደነበር አንስተዋል።

በዛሬው ዕለትም የተደረሰው ሥምምነት ከዚህ ቀደም ሲደረግ ለነበረው ድጋፍ ማስፋፊያ መሆኑን ጠቁመው፤ የተፈናቃዮቹን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ድጋፍ በሌሎች አካባቢዎች በተመሳሳይ መልኩ እንዲደረግ ኮሚሽኑ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች የሚከሰቱ ችግሮች በሰዎች ላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።(ኢዜአ)