የኢህአዴግ ምክር ቤት በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገለጸ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው  የኢህአዴግ ምክር ቤት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገለጸ፡፡

ኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በላከው የሀዘን መግለጫ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ጥልቅ ሀዘኑን ገልጿል።

ምክር ቤቱ የህዳሴ የግድብ ግንባታ ከዳር በማድረስ የኢንጂነር ስመኘውን ህልምና ራዕይ ዕውን እንደሚሆን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዕውን እንዲሆን ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነትንና አደራ ለመወጣት በከፍተኛ  ቁርጠኝነት ማገልገላቸውን የገለጸው መግለጫው፤ ኢንጅነር ስመኘው ትጋታቸውና ጽናታቸው በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ታትሞ እንደሚኖርም ነው ያስታወቀው።

ኢንጂነር ስመኘው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ባደረጉት ርብርብም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሁን የደረሰበትን ደረጃ እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በተጨማሪ በሌሎች የኃይል ማመንጫ ግድቦችም አሻራቸውን አሳርፈዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስትም ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር ለማድረስ የሚያደርጉትን ርብርብ በማጠናከር የኢንጂነር ስመኘው በቀለን ህልምና ራዕይ ዕውን እንደሚያደርጉ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በታታሪው፣ የጽናትና የቁርጠኝነት ተምሳሌቱ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጆቻቸው እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝቷል። (ኢዜአ)