የኢንጂነር ስመኘው በቀለ የቀብር ስነ ስርዓት በቅድስት ስላሴ ካቴድሪያል ቤተክርስቲያን ተፈፀመ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ የኢንጂነር ስመኘው በቀለ የቀብር ስነ ስርዓት በቅድስት ስላሴ ካቴድሪያል ቤተክርስቲያን ተፈፀመ።

በቀብር ስነ ስርዓቱ ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ማትስያስና ሌሎች ሊቀነ ጳጳሳት በተገኙበት የፀሉት ስነ ስርዓት ተካሄዷል።

የአንጅነር ስመኘው አስክሬን በርካታ ህዝብ በተገኙበት በመስቀል አደባባይ የክብር የሽኝት ስነ ስርዓት ተካሂዶለታል ።

የቀብር ስነ ስርዓቱም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ
መኮንንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባደረጉት ንግግር እንደ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሰርቶ መሞት ትልቅ ነገር ነው ያሉ ሲሆን፥ የህዳሴን ግድብ እንደወለዱት ነው የሚቆጠረው ብለዋል።

የቀብር ስነ ስርዓቱ ለአንድ የልማት አርበኛ ጀግና በሚደረግ ስነ ስርዓት ተከናውኗል።

በቀብር ስነ ስርዓቱ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተወካያቸው፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና የክልል መንግስታት በወቅቱ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።

ኢንጅነር ስመኘው ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ማለዳ ላይ መስቀል አደባባይ በሚያሽከረክሯት መኪና ውስጥ ሞተው መገኘታቸው ይታወሳል።

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ አሁን ሰሜን ጎንደር እየተባለ በሚጠራው ዞን ጠዳ ወረዳ ማክሰኚት ከተማ በ1958 የተወለዱ ሲሆን፥ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባትም ነበሩ።

የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በእንፍራንዝ የተከታተሉት ኢንጂነር ስመኘው፥ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወልድያ ከተማ ተከታትለዋል።

ከዚያም 1989 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምህንድስና ትምህርት ክፍል የመጀመያ ዲግሪያቸውንም አግኝተዋል።

ከ1978 ጀምሮ በቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽን ይሰሩ የነበረ ሲሆን፥ እስክ 1986 ዓ.ም በተቋሙ የኮተቤ ማሰልጠኛ መምህር የነበሩ መሆኑ ነው የተገለጸው።

ኢንጂነር ስመኘው ከ1986 እስከ 1988 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጥራት ቁጥጥር ኢንስፔክተር፣ ከ1990 እስክ 1991 ዓ.ም በቀድሞ የኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽኑ የስልጠና መምህር፣ ከ1992 እስከ 1996 ዓ.ም በግልገል ጊቤ ቁጥር አንድ የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከቢሮ መሀንዲስ እስከ ዋና መሀንዲስነት በመሆን አገልግለዋል ።

ከዚያም ከ1998 እስከ 2002 አ.ም የግልገል ጊቤ ቁጥር ሁለት ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ሰርተዋል።

በመጨረሻም ከ2003 ዓ.ም  ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ነበሩ።(ኤፍቢሲ)