የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ህልፈት ምክንያት የተሰማቸቸውን ጥልቅ ሃዘን ገለጹ ።
በተለያዩ ሰባት ሐይማኖቶች የተውጣጡት የሃይማኖት አባቶቹ በዛሬው ዕለት በጽህፈት ቤታቸው በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ህልፈት ምክንያት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል ።
በተጨማሪም አባቶቹ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡት ላጡትና ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች በሙሉ መጽናናትን ተመኝተዋል ።
የሃይማኖት አባቶቹ በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉት ግጭቶችን በአጭር ጊዜ እንዲቆምና ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ሊፈታ እንዲችል በተጠና መንገድ ምላሽ እንዲሠጠውም ጠይቀዋል ።
በተለይ በጉጂና ጌዲኦ አካባቢዎች በተፈጠሩት ግጭቶች ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው በተለያዩ የመጠሊያ ጣቢያዎች የሚገኙትን ዜጎች አስፈላጊው ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ያሳሰቡት የሃይማኖት አባቶቹ በልማት ድርጅቶቻቸው አማካኝነት ለተፈናቃዮቹ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል ።
በአሁኑ ወቅት በመንግሥት በኩል እየተደረገ ያለውን የይቅርታ ፣ የእርቅ ፣ የምህረት፣ የፍቅርና የአንድነት አስተሳሰብ በሃይማኖትም የሚደገፍ በመሆኑ መንግሥት የህግ የበላይነትን በሚያስከብር መልኩ ለዜጎች ሰላም መጠበቅ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል ።
በአገሪቱ እያገለገሉ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች በተለያዩ አካባቢዎች ዘርንና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ወደባሰ ደረጃ እንዳይሸጋገሩ የተለመደ መንፈሳዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም የሃይማኖት አባቶቹ በመግለጫው ጥሪ አቅርበዋል ።