ሁላችንም ደስ ብሎናል” – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ኢትዮጵያ መመለስን አስመልክቶ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል የአቀባበል ስነ ስርዓት ተከናውኗል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በአቡነ መርቆርዮስወደ ኢትዮጵያ መመለስ ሁላችንም ተደስተናል ብለዋል።

በተጨማሪም 26 ዓመታት ተራርቃ የቆየችውን ቤተክርስትያን አንድ በማድረጉ አምላክን እንደሚያመሰግኑም ነው የተናገሩት።

በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን የጸሎትና የቅዳሴ ስነስርዓት የተከናወነ ሲሆን፥ ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ወረብ አቅርበዋል፤ ቅኔም ዘርፈዋል።

በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስንና ብጹዓን አባቶችን ከስደት መመለስን ተከትሎ የሀገረ ስብከት መሪዎች፣ የአድባራትና የገዳም አስተዳዳሪዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እንዲሁም በርካታ ምዕመናን በቤተክርስቲያን ተገኝተዋል።

በተጨማሪም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የተለያዩ የእምነት አባቶች እና አምባሳደሮች በስነ ስርዓቱ ላይ ታድመዋል።

እንዲሁም ከጸሎት ስነስርዓት በኋላ ሁለቱም ሲኖዶሶች በዕርቅ ሂደቱ ያለፉበትን ለምዕመናኑ አንብበዋል።

ብጹዕ አቡነ አብርሃም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙት ሲኖዶሶች ሦስት ሦስት አባቶቸን በመወከል የዕርቅ ሂደቱ መጀመሩንም ገልጸዋል።

በዚህም የልዑካን ቡድኑን አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው የዕርቅ ሂደቱን ለመደገፍ የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ መግለጻቸውንም አባቶች ጠቅሰዋል።

ይህንንም ተከትሎ በሀገር ቤት የነበረው ሲኖዶስ ሐምሌ 11 ወደ አሜሪካ ያቀና ሲሆን፥ በዳላስ አውሮፕላን ማረፊያም በዚያ ያሉት አባቶች ባልተለመደ መልኩ ደማቅ አቀባበል ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ሁለቱም የሲኖዶስ ተወካዮች ከተገናኙ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የመክፈቻ ጸሎትና የመዝጊያ ጸሎት የት ማድረግ እንደነበረባቸው ከወሰኑ በኃላ በሁለቱም ሲኖዶሶች በኩል ስድስትና ስምንት አጀንዳዎች መቅረባቸውን ተናግረዋል።

በመጨረሻም አጀንዳዎቹን ወደ ስድስት ዝቅ በማድረግ ውይይታቸውን በዝግ ስብሰባ ማድረጋቸውን ነው ያስታወቁት። 

በተለያየ ዓመት ለአራት ጊዜያት ያህል የእርቅና የሰላም ሂደቱ መሞከሩን ገልጸው የአሁኑ ግን በተጀመረ በሦስት ሰዓታት መጠናቀቁን አብስረዋል።

ብጹዕ አቡነ አብርሃም የተስማሙባቸውን ውሳኔዎች ጠቅሰዋል በዚህም በሁለቱም ሲኖዶስ መካከል የተደረሰውን የዕርቀ ሰላም ውህደት ፍጹም ለማድረግ የሚተዳደሩበትን ቅድመ ሁኔታ ለማዘጋጀት ሁለቱም ሲኖዶሶች ተስማምተዋል።

እንዲሁም በውጭ የሚገኙ ቤተክርስትያናት በስርዓተ ቤተክርስትያን ቅኖናዊ አስተዳደር መሰረት በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንዲመሩ መወሰኑም ነው የተገለፀው።

ብጹዕ አቡነ አብርሃም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከመጀመሪያ ጀምሮ ጉዳዩን በመከታተላቸው ምስጋና አቅርበዋል። እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስታቸውን ወክለው ዝቅ ብለው ይቅርታ ጠይቀዋል ይህንንም አስመልክቶ ሲኖዶሱ ከፍ ያለ ምስጋናውን አቅርበዋል።

በውጭው ሲኖዶስ በኩል የተወከሉት መላዕከ ህይወት ብርሃን የሰላምና የአንድነትና ጉባዔ ያደረገውን በአጭሩ ከመላው ዓለም ከአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ከናዳ ከኢትዮጵያ ተቋቁሞ ለፍጻሜ ማድረሱን ገልጸዋል።

ዛሬ አንድ ለሆኑት ትላንት ሁለት በነበሩት ሲኖዶሶች መካከል ሦስተኛ አደራዳሪ ሳይገባ በራሳቸው የዕርቀ ሰላሙን መፈጸሙን አስታውቀዋል።

የአቡነ መርቆርዮስ ተወካይ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ኤልያስ "ነገርን ሁሉ ውብ አድርጎ ሰራው " የሚለውን የጠቢቡ ሰለሞንን መልዕክት በማንሳት ዛሬ የሆነው ነገር ሁሉ ምስጢር ነው ብለዋል።

አቡነ ኤልያስ የቤተክርስትያኑን ታሪክ በማንሳት ለምዕመናኑ ሰፊ ንግግር አድርገዋል።

እንዲሁም መስከርም ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ያሰቡ እንደነበረ ጠቅሰው ሆኖም በፈጠሪ ፍቃድ ቤተክርስትያን ዕለቱን ሰማዕቱ መርቆርዮስ እያለች

በምታስብበት ቀን አቡነ መርቆርዮስ በመግባታቸው ትልቅ ምስጢር መያዙን ገልጸዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባደረጉት ንግግር "ወንድሞች በህብረት ቢኖሩ መልካም ነው" የሚለውን መልዕክት በማንሳት ዛሬ ታላቅ ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል፡፡

እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳዩት የማቀራረብ ሂደት ባለፉት 45 ዓመታት ባልታየ ሁኔታ በሰሩት ስራ የቤተክርስቲያኒቱ ዋነኛ ታሪክ አካል መሆናቸውን ጠቅሰው በጸሎታቸውም እንደምታስባቸው ገልጸዋል። ወንድማማችነታችንና መንፈሳዊነታችንን አጸንተን ከማቆየት ምን እንከፍለዋለን ነው ያሉት።

አቡነ ማትያስ ህዝበ እግዚአብሄር የሆነው ምዕመን እኛ ክልተረዳዳን ጽኑ ፈተና ያገኘዋል በዚህም ለቤተክርስትያኑ ጽናት እየተመካከርን ስራውን የበለጠ እያሻሻልን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንመራዋለን የሚል ጹኑ እምነት አለን ብለዋል፡፡(ኤፍቢሲ)