የኢንጂነር ስመኘው ቤተሰብን ለመደገፍ የባንክ ሂሳብ ተከፈተ

የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ቤተሰብን ለመደገፍ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የበላይ ጠባቂነት በኢንጂነር ስመኘው ልጆችና ቤተሰብ በጋራ የሚንቀሳቀስ የባንክ ሂሳብ መከፈቱን የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሂሳቡ የተከፈተው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወጂ ቅርንጫፍ አዲስ አበባ እንደሆነና የሒሳብ ቁጥሩም 1000254503812 መሆኑን ተገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ ለዋልታ በላከው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ከውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር፣ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት፣ ከመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ከኢንጂነር ስመኘው በቀለ ቤተቦች የተውጣጡ አባላት የሐውልት አሰሪ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡

በቀጣይም የኢንጂንር ስመኘውን ሥራዎች ሕያው ለማድረግ በሐይድሮፓወር ዙሪያ ለሚያጠኑና ከፍተኛ ውጤት ለሚያገኙ ተማሪዎች “ስመኘው በቀለ አዋርድ” በሚል በየዓመቱ ሽልማት ለመስጠት እንዲሁም በሐይድሮፓወር ዙሪያ ትምህርታዊ ጉባዔ ለማካሄድና የመሳሰሉትን ሥራዎች ለማከናወን እንደታቀደም በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሐምሌ 19፣ 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ በጥይት ተመተው  ሕይወታቸው እንዳለፈ ይታወሳል፡፡