ኮሚሽኑ ተፈናቃዮች ባሉበት ድጋፍ ስለሚሰጥ ወደ ተቋሙ በመሄድ ለወጪና እንግልት እንዳይዳረጉ አሳሰበ

የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ተፈናቃዮች ባሉበት ቦታ በመንቀሳቀስ ድጋፍ የሚሰጥ በመሆኑ ወደተቋሙ በመሄድ አላስፈላጊ ለሆነ ወጪና እንግልት እንዳይጋለጡ አሳሰበ።

ኮሚሽኑ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮች አስፈላጊው ሁሉ እየተደረገላቸው እንደሆነ ገልጿል።

የኮሚሽኑ የሎጅስቲክና አቅርቦት ዳሬክተር አይሩስ ሀሰን እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ከክልሎች በሚቀርብ የተረጂውች ቁጥር ልክ ድጋፍ እየተደረገ ነው።

በኮሚሽኑ የሚደረገው ድጋፍ ተፈናቃዮች ባሉበት አስፈላጊውን የቁሳቁስና የምግብ ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም በተሳሳተ መልኩ አንዳንድ ተፈናቃዮች በቀጥታ አዲስ አበባ በመምጣት ከኮሚሽኑ ዋና መስሪያ ቤት በመምጣት ስራው ላይ ጫና እየተፈጠረበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ለተፈናቃዮች መደረግ ያለበት ድጋፍ ሁሉ ባሉበት የሚቀርብ በመሆኑ ተፈናቃዮቹ አዲስ አበባ ድረስ በመጓዝ አላስፈላጊ ለሆነ ወጪና እንግልት መዳረግ እንደሌለባቸው አቶ አይሩስ አስገንዝበዋል።

ኮሚሽኑ በሚከተለው አሰራር መሰረት ክልሎች በሚያደርጉት የቅድመ ዳሰሳ ጥናት ላይ ተመስርቶ በሚቀርበው የተረጂዎች መጠን ድጋፍ የሚያደርግ እንደሆነም አስረድተዋል።

ከዚህ አሰራርና ስርዓት ውጪ ኮሚሽኑ ለመስተናገድና ድጋፍ ለማድረግ የሚቸገር መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ተፈናቃዮች በዘላቂነት እንስኪቋቋሙ ድርስ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለዚህም ለስድስት ወር የሚበቃ የምግብና የቁሳቁስ ክምችት እንዳለው ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያሉት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተፈናቃዮች ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። (ኢዜአ)