የሐረሪ ከተማ ነዋሪዎች በቆሻሻ ክምር መማረራቸውን ገለጹ

በሀረሪ ከተማ የሚገኘው የቆሻሻ ክምር በወቅቱ ባለመነሳቱ ምክንያት በጤናችን እና በሥራችን ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረብን ነው ሲሉ የሀረሪ ከተማ ነዋሪዎች  ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በቆሻሻው ምክንያት እስከ አንድ ወር ለዘለቀ ጊዜ አገለግሎት መስጫ ድርጅቶቻቸውን ለመዝጋት እንደተገደዱም ተናግረዋል፡፡

የሀረሪ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ኑረዲን ችግሩ ከተጨማሪ ካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ የተከሰተ እንደሆነና ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከባለድርሻ አካላት ጋር ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አስተዳደሩ ከአራት ዓመታት በፊት በ11 ሄክታር መሬት ላይ ቆሻሻውን ለማከማቸትና ካሳ ለሚገባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ክፍያ ቢፈጽምም ነዋሪዎቹ የካሳው መጠን አነስተኛ ነው በሚል መነሻ በፈጠሩት ቅሬታ ቆሻሻውን ሰብስቦ በተዘጋጀው ቦታ ለማከማቸት እንዳልተቻለ ተጠቁሟል፡፡

የሀረሪ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ለዋልታ የላከው መረጃ እንደሚያመለክተው ችግሩን በአንድ ሳምንት ውስጥ ለመፍታት ኮሚቴው እየሰራ እንደሆነ ታውቋል፡፡