1,439ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በአዲስ አበባ ስታዲየም ተከበረ

1 ሺህ 439ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል  በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ ስታድየም  በስግደት ተከበረ።

በዛሬው ዕለት የሀይማኖት አባቶችና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጀነር ታከለ ኡማን ጨምሮ በርካታ እንግዶችና የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት ነው የተከበረው።

በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ መሀመድ ሸሪፍ ሀሰን፥ የአረፋ በዓል የአለም ሙስሊሞች በአንድነት ዘር፣ ቋንቋ፣ ብሄር፣ቀለም ፆታ ሳይለያያቸው አምላካቸውን የሚያስታውሱበትና የሀጅ ስነ ስርዓትን የሚያከብሩበት ታላቅ የእስልምና በዓል መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ በሀገሪቱ እየተገኘ ያለውን የአንድነት፣ የፍቅር፣ የነፃነት መንገድ በአክብሮት መጠበቅና ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ገልፀዋል።

እንዲሁም ይህ ታላቅ በዓል ሲከበር የተፈናቀሉ ወገኖችን በማቋቋምና ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ በማድረግና በማካፈል መሆን እንደሚገባ  ሼህ መሀመድ ሸሪፍ ሀሰን አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተወካይ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ ፥ አረፋ የሰላም፣ የደስታ እና የብስራት ቀን  ነው ብለዋል።

እስልምና ተንኮል፣ ጥላቻ፣ በቀል እና መገዳደልን ያወግዛል ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እንዲሪስ እስልምና  የሰላም ፣ አንድነት፣ መከባበር፣ መተባበር  እና መተዛዘን መፍለቂያ  መሆኑን ተናግረዋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እንዲሪስ   የሙስሊም ፀባይ አንድነት እና ሰላም በመሆኑ ሰላምን ማክበርና ልማትን ማፋጠን  እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በበዓሉ ላይ  በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው፥ በዓሉ የከተማዋ ተደማሪ የልማት ኃይል እና የለውጥ አጋር እርምጃ የሆነው ነገር ግን ለዓመታት ተከፋፍሎ የቆየው የሙስሊም ማኀበረሰብ አንድነቱን ለማጠናከር በጋራ መንቀሳቀስ በጀመረበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ በመሆኑ  ድምቀቱን እንደ ንጋት ብርሃን ያጎላዋል ብለዋል።

አንድነቱ ለከተማዋ ውበት  ፣ሃብት እና  ለኢትዮጵያዊነት አንዱ መገለጫ ምልክት እንደሆነ ነው ኢንጂነር ታከለ ኡማ  የገለፁት።

በዓሉ በባህርዳር፣ መቐለ፣ አደማ፣ ድሬደዋ፣ ሀረር ጨምሮ በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች በዓሉ በስግደት ሥነስርዓት ተከበሯል። (ኤፍቢሲ)