ኢትዮጵያ የምትልከው የማር ምርት በጥራት ጉድለት ምክንያት መጠኑ እየቀነሰ ነው

ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልከው የማር ምርት በጥራት ጉድለት ሳቢያ መጠኑ በየጊዜው ቅናሽ እያሳየ መሆኑ ተገለጸ።

በዘርፉ የሚታየውን የጥራት ችግር ለመፍታትም የጥራት ቁጥጥር የሚሠጡ ተቋማትን አቅም የሚያሳድግ ፕሮጀክት በዘርፉ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ነው ብሄራዊ የጥራት መሠረተ ልማት ፕሮጀክቱ የተዘጋጀው፡፡

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ወንድወሰን ፍስሃ እንዳሉት ሚኒስቴሩ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በጥራት ላይ በተደረገ ጥናት መሠረት ፕሮጀክቱ ተቀርጿል።

አገሪቱ እ.ኤ.አ በ2013 ከ880 ቶን በላይ የማር ምርት ለውጭ ገበያ ብታቀርብም ወደ ውጭ የምትልከው ምርት እየቀነሰ መጥቶ ባለፈው ዓመት የተላከው የማር ምርት ወደ 500 ቶን ሊወርድ ችሏል።

ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር የሚደገፈው ይህ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት በእርሻ ምርቶች፣ ጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ዘርፍ ላይ የሚታዩ የጥራት ችግሮችን ለማሻሻል የተዘጋጀ ነው።(ምንጭ:ኢዜአ)