የ2010 ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የፈተና ውጤት እስከ አርብ ይፋ ይደረጋል

የ2010 ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የፈተና ውጤት እስከ  ቀጣዩ አርብ ድረስ ይፋ እንደሚሆን የሀገር ዓቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ አስታውቋል።

የኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ገብረእግዚአብሔር እንደገለጹት ኤጀንሲው የ ፈተናውን  እርማት በማጠናቀቅ መረጃውን በአጭር ጽሁፍ እና በድረ-ገጽ በጥራት ለማሰራጨት ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየተሰራ ነው፡፡

ኤጀንሲው እስካሁን የትኛውንም የውጤት ማሳወቂያ ዘዴ በመጠቀም ውጤት እንዳላወጣና ተማሪዎችም በኤጀንሲው ስም በሚወጡ የተሳሳቱ መረጃዎች እንዳይታለሉም ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡
ውጤቱን ይፋ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች መጠናቀቃቸውንና እስከ መጪው አርብ ድረስ ውጤቱ እንደተለመደው በኤጀንሲው ድረ-ገፅና በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ይፋ ይደረጋልም፡፡
ተማሪዎች የለፉበት ውጤት እንዳይሳሳት በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ አርአያ የ2010 ዓ.ም የ10ኛ ክፍል የፈተና ውጤትን ተማሪዎች በትዕግስት እንዲጠባበቁም ጠይቀዋል፡፡