የአዲስ ዓመት የበጎ አድራጎት ተግባራት እንደ ባህል ተቆጥረው ሊቀጥሉ ይገባል -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ደመቀ መኮንን

መጪውን አዲስ አመት ምክንያት በማድረግ የተጀመሩ የበጎ አድራጎት ተግባራት እንደ ባህል ተቆጥረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለዋልታ ቴሌብዥን ተናግረዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱን አመት በፍቅር ተደምረን በይቅርታ እንሻገር በሚል መሪ ቃል ስንቀበል በተግባር እንዲሆንም ለህብረተሰቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አመት ስጦታ ለእናት ሀገሬ በሚል መሪ ቃል መጪውን አዲስ አመት  ለመቀበል የተለያዩ በጎ አድራጎት ተግባራት በዘመቻ መልክ ለአቅመ ደካሞችና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ቤት ከማደስ ጀምሮ፣ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስና አልባሳት በመግዛት ፣ በደም ልገሳና በመሳሰሉት በጎ አድራጎት ተግባራት ልገሳው መለመድ ያለበት ተግባር ነው ብለዋል አቶ ደመቀ ።

የበጎ አድራጎት ስራዎች  በተለያዩ ተግባራት የሚገለፅ ሲሆን አዲሱን አመት በዚህ እሳቤ ለመቀበል በተግባር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የሚያስደስቱ  ናቸው በማለት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገልፀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም  ክረምትን ምክንያት በማድረግ ተማሪዎች በእረፍት ጊዜያቸው የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን  ያስታወሱት አቶ ደመቀ ይህ ተግባር እያደገና  እየሰፋ መምጣቱን ጠቁመው ድርጊቱ  በዘመቻ መልክ ከመሆን ባለፈ እንደ ባህል ሊቀጥል እንደሚገባ  አስገንዝበዋል፡፡

በበጎ አድራጎት ተግባራት እየተሳተፉ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች፣አርቲስቶች፤ወጣቶች እያከናወኑት ያለው ተግባር የሚያኮራ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ተከትሎ ፣የመንግስት ተቋማት፤ የሃይማኖት ተቋማት በጋራ በመሆን ባህል ሆኖ እንዲቀጥል መስራት እንዳለባቸው ተቅሰዋል፡፡

አያይዘውም የዘንንድሮውን አዲስ አመት ለየት የሚያደርገው ቀደም ብሎ ፍቅርን ይቅርታን መደመርንና አንድነትን  መሠረት አድረገን እየተጓዝን በመሆኑ አዲሱ አመት የበለጠ ጎልቶ የምናይበነት  ነው ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አዲሱን አመት በፍቅር ተደምረን በይቅርታ እንሻገር በሚል መሪ ቃል ስንቀበል በተግባር እንዲሆን  በመግለፅ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡