ተወዳጁ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ወይም በቅጽል ስሙ ቴዲ አፍሮ ከባለቤቱ ጋር በመሆን በቡራዩና አካባቢዋ ጉዳት ለደረሰባቸው እንዲሁም ለተፈናቀሉ ዜጎች የ 1ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ ።
አርቲስት ቴዎድሮስ በዛሬው ዕለት ከባለቤቱ ወይዘሮ አምለሰት ሙጬ ጋር በመሆን በመድሓኒአለም ትምህርት ቤት ተጠልለው የሚገኙትን ተፈናቃዮች በጎበኘበት ወቅት ነው የ 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገው ።
አርቲስት ቴዎድሮስ ተፈናቃዮችን ከጎበኘ በኋላ ለዋልታ ቴሌቭዠን እንደገለጸው በሁኔታው እጅግ ማዘኑንና የአዲስ አበባ ህዝብ ለተፈናቃዮች እያደረገ ላለው ድጋፍ ታላቅ ምስጋና ይገባዋል ብሏል ።
አርቲስት ቴዎድሮስ ያደረገውን የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የተቀበለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ አርቲስት ቴዎድሮስ ለተፈናቃዮች ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርቧል ።
ከቡራዩ አካባቢ ለተፈናቀሉ ዜጎች የተሠጠው የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍም በመድሐኒዓለም ትምህርት ቤት ለተጠለሉ ተፈናቃዮች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እንደሚውል የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል ።
እስካሁን ድረስ በመድሓኒዓለም ትምህርት ቤት ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ 3 ሺህ የሚሆን ፍራሽና ብርድ ልብስ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች መሠጠቱም ተመልክቷል ።
በቡራዩ ከተማ፣ ከተና አሸዋ ሜዳ አካባቢዎች በደረሰው አደጋ እስካሁን ድረስ 12 ሺህ ያህል ዜጎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን 1ሺህ 700 የሚሆኑ በመድሓኒአለም ትምህርት ተጠልለው ይገኛሉ ።