የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ ቅርሶችን ለአለም ለማስተዋወቅ እየሰራ ነው

የኢፌድሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በኢትዮጽያ የሚገኙ የተለያዩ የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ ቅርሶችን ለአለም ለማስተዋወቅ እየሰራ ይገኛል፡፡

በየአመቱ መስከረም 17 በሚከበረው የአለም የቱሪዝም ቀንን በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በማክበር ኢትዮጽያን በቱሪዝም ዘርፍ ባላት ሀብት ቀዳሚ ለማድረግ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አንዱ ነው፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች አለመኖርና የበጀት እጥረት እንዳለበትም የሚኒስቴሩ የህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛከኝ አባተ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ከባለሙያ አለመኖር ጋር ተያይዞ ከውጭ ሀገራት ባለሙያ በማስመጣት የሚደረገው የጥገና ስራ ለዘርፉ ከሚውለው  ከፍተኛ በጀት እንደሚወስድ የሚታይ እውነታ እንደሆነም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል ።

በዚህም ምክንያት ስጋት ላይ የሚገኙትን ቅርሶቻችንን በሙሉ ጥገና ማከናወን አልቻልንም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴርና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን በቅርስ ጥገናና ጥበቃ ዙሪያ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል ምክክር መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

ሁሉም ዜጋ በሀገሪቱ ያሉ ቅርሶችን የመጠበቅ ሀላፊነት አለበትና በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልግ ማንኛውንም ዜጋ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በር ክፍት ነውም ብለዋል፡፡