11 ሺህ 902 የቡራዩ ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያ ቀያቸው ተመለሱ

ከቡራዩ ተፈናቅለው ከነበሩት 15 ሺህ 86 ዜጎች መካከል በተፈጠረው መረጋጋት 11 ሺህ 902 የሚሆኑት ወደ መኖሪያ ቀያቸው መመለሳቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ቡራዩ ከተማ በተፈጠረው መረጋጋት በአስተዳደሩ አማካኝነት 11 ሺህ 902 ያህል ተመልሰዋል፡፡

በመሆኑም በአዲስ አበባ በአሁን ወቅት በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙት 1 ሺህ 514 መሆናቸው ተገልጿል።

የከተማዋ አስተዳደር ላለፉት ስምንት ቀናት ተፈናቃዮች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያነት የቆዩባቸውን ዘጠኝ ትምህርት ቤቶች በትላንትናው እለት ጽዱ በማድረግና በዛሬው ዕለት ለሚጀምረው የመማር ማስተማር ዝግጁ ተደርጓል ተብሏል።

በስድስቱ ክፍለ ከተሞች ከነበሩት 20 ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎች መካከል 17ቱ ተዘግተው ቀሪዎቹ ተፈናቃዮች በሶስት የመጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ ተብሏል።

በቀሪዎቹ ሶስቱ መጠለያ ጣቢያዎቹ ለተፈናቃዮቹ ሁሉን አቀፍ አገልግሎትና መረጃ የሚሰጥ የጣቢያ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፥ አስፈላጊውን አገልገሎት በቅርበት መስጠቱን እንደሚቀጥል ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለተፈናቃዮቹ ባለፉት ቀናት ሲያደርጉት ለቆዩት ድጋፍ የከተማ አስተዳደሩ ምስጋና አቅርቧል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)