ምዕመናን የመስቀል በዓልን በመተሳሰብ እንዲያሳልፉ ቤተክርስቲያኗ ጥሪ አደረገች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን  ጠቅላይ ጽህፈት ቤት በዛሬው ዕለት በሠጠው መግለጫ  ምዕመናን የመስቀል በዓልን በመተሳሰብ ማሳለፍ እንዳለባቸው ጥሪ አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲያስቆሮስ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረውን የመስቀል በዓልን አስመልክቶ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ብጹዕ አቡነ ዲያስቆሮስ ለመላው ክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ካስተላለፉት በኋላ ሁሉም የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን በመተሳሰብ ማሳለፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡  

በዓሉ በሰላም እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪያቸውን ያስተላለፉት ብጹዕ አቡነ ዲያስቆሮስ ለበዓሉ አከባበር የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ፣ ቡራዩ. ኢትዮጵያ ሶማሌ እና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ የተፈጠሩ ግጭቶችን ቤቴክርስቲያኗ በፅኑ እንደምታወግዝ ገልጸው ሁሉም ስለሀገራችን ማሰብ እንዳለበት እና መንግስትም መሰል ችግሮች እንዳይደገም ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ቤቴክርስቲያኗ ትጠይቃለች ብለዋል፡፡

ቤተክርስቲያኗ ማዕደ ሰፊ መሆኗን በማንሳት በዓሉ ስናከብር የመስቀሉ መገለጫ ያልሆኑ ድርጊቶች ሊኖር እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡

አባቶቻችን ያወረሱትን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተግባር በማንጸባረቅ ሀገር ተረካቢ ወጣት የተረጋጋች ሀገርን ለመፍጠር ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡ 

ብጹዕ አቡነ ዲያስቆሮስ አያይዘውም መንግስትም ሆነ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገርና ለህዝብ አንድነት፣ ሰላም እና እድገት ቅድሚያ በመሥጠት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የኃይማኖት መሪዎች ከመንግስት እና ከቤተሰብ ጋር በመሆን ወጣቱን የመምከር ስራ እንዲሰሩም ጠይቀዋል፡፡