የኢሬቻ በዓል ከኦሮሞ ሕዝብ አልፎ በሁሉም የአገሪቷ ዜጎች ዘንድ እንዲታወቅ እንሰራለን-የበዓሉ ታዳሚዎች

 የኢሬቻ በዓል ሰላማዊነቱንና ትውፊታዊ ባህሪውን ጠብቆ ከኦሮሞ ሕዝብ አልፎ በሁሉም የአገሪቷ ዜጎች ዘንድ እንዲታወቅ እንደሚሰሩ የበዓሉ ታዳሚዎች ተናገሩ።

የዘንድሮ ኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ በሚሊየን የሚቆጠር ህዝብ በተገኘበት በተለያዩ ባህላዊ ክንውኖች ደምቆ ተከብሯል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎች እንደሚሉት ወደ ፊት በዓሉ መሰረቱ ሰላምና አንድነት መሆኑ ታውቆ ሌሎች የአገሪቷ ህዝቦችም እንዲያውቁት በትኩረት ይሰራል

በዓሉ ላይ ለሶስተኛ ጊዜ የታደመው የምስራቅ ወለጋው ወጣት ቤኛ ዋቁማ ከሁለት ዓመት በፊት ክብረ በዓሉ ላይ በተፈጠረ አደጋ የሁለት ጓደኞቹ ህይወት እንዳለፈ ያስታውሳል።

ወጣቱ የዘንድሮ ኢሬቻ በዓል የተለየና በአብዛኛው ታዳሚ ዘንድ ያለስጋት በተረጋጋ መንፈስ የተከበረ በዓል በመሆኑ እጅግ እንደተደሰተም ተናግሯል።

ይህ በዓል ወደ ፊትም ያለማንም ጣልቃ ገብነት ነጻነቱን ጠብቆ፣ ባህላዊ እሴቶቹ ሳይበረዙ እንዲከበርና በሌሎችም ዘንድ እንዲታወቅ ለማድረግ የበኩሉን እንደሚወጣም ገልጿል።

ሌላው ከምዕራብ ሸዋ ሜታ ሮቢ ወረዳ የመጣው አበራ ፈይሳ የዘንድሮ ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ አንድነት እጅግ በጠነከረበት ወቅት የተከበረ በመሆኑ ልዩ በዓል ነው ብሏል።

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከበሩት የኢሬቻ በዓላት ህዝቡ በከፍተኛ ስጋትና ጭንቀት ውስጥ ሆኖ ከባህላዊነቱም በወጣ መልኩ ነበር በማለት አስታውሷል።

ይህ በዓል የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር በተለይ ወጣቱ በዓሉ እሴቱንና ሰላማዊነቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ሊሰራ ይገባል ብሏል።

ከአማራ ክልል ኦሮሞ ልዩ ዞን ከሚሴ አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓሉ ላይ የታደሙት ጎልማሳ ሃሳን ኑር አህመድ ይህ ቀን እንዲህ ሰላማዊ ሆኖ በማየቴ ደስተኛ ሆኛለሁ ይላል።

ይህም ሆኖ በዓሉ ከዚህ በኋላ እንደ ጥንት መሰረቱን ሰላምና አንድነት ላይ አድርጎ የሁሉም ህዝቦች እንዲሆን መጠበቅና መንከባከብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ለአምስተኛ ጊዜ በዓሉ ላይ መታደሙን የተናገረው የምዕራብ አርሲው አብደላ ዴቢሶ በበኩሉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓሉን በስጋት አክብሮ ሲመለስ እንደነበረ ይናገራል።

አብደላ ዘንድሮ ያለምንም ስጋት በዓሉን ማክበሩን ተናግሮ ይህ የአንድነትና የሰላም መሰረት የሆነ በዓልን ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር መጋራት ያስፈልጋል ሲል ያስረዳል።

ዘንድሮ የኢሬቻ በዓል ላይ ከወትሮ በተለየ መልኩ ከሲዳማ፣ ሃላባ፣ ኮንሶ፣ ቡርጂ፣ ወላይታና ከጋሞ የተወከሉ ወጣቶችና የአገር ሽማግሌዎች ታድመዋል።(ኢዜአ)