የተረጋጋና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ሁሉም የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተረጋጋና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ሁሉም የበኩሉን ጥረት ማድረግ እንዳለበት የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ሞኮንን አሳሰቡ።

የትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮ ዓመት ሰላማዊ የመማር ማስተማርን ለማረጋገጥ የሚያስችል ውይይት ከሐይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሎዎች፣ ከአባ ገዳዎችና ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

በዚህ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ እንደገለጹት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማሪያ፣ የምርምር፣ የጥበብ መፈለጊያ፣ ያለፉ በጎ የታሪክ ምዕራፎችን ማስቀጠያና ስህተት የተደረገባቸውን ደግሞ እንዳይደገሙ ጥረት የሚደረግበት ቦታ ነው።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በስብዕናቸው የተመሰገኑና ለሌላው አርአያ መሆን ሲገባቸው የልዩነትና የብጥብጥ መለያ መሆን የለባቸውም ብለዋል።

እንደ አቶ ደመቀ ገለጻ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዝግጅት ጊዜ ተማሪዎችን ከመጥራታቸው በፊት ያላቸውን ዕድሎችና ተግዳሮቶች ለይተው ጥፋቶችን መግታት የሚችሉበትን፣ የህግ የበላይነት የሚከበርበትን፣ መብትና ግዴታውን የሚያውቅ ትውልድ ለመፍጠር መስራት ይኖርባቸዋል።

ለዚህም ቤተሰብ፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ዩኒቨርስቲዎቹ የሚገኙባቸው አካባቢ ማህበረሰብ አባላት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮችና ከንቲባዎች የውስጥ አደረጃጀትን በማጠናከር ተማሪዎች ከሚማሩበት አካበቢ ኀብረተሰብ ጋር እንዲዋሀዱና የጋራ መስተጋብር እንዲኖራቸው የሚያስችሉ የተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባም አመልክተዋል።

የተማሪዎች ምክንያታዊነትና የዴሞክራሲ ባህልን በማዳበር ለአገራዊ ለውጥ እንዲተጉ፣ እንዲወያዩና ስለ አገራቸው እንዲያውቁ የሚያስችል የእርስ በርስ የውይይትና የክርክር መድረኮችን ማዘጋጀት ተገቢ እንደሆነም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ጠቁመዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኮሙዩኒኬሽን ግንኙነትን በማህበራዊ ሚዲያ በማጠናከር ተማሪዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ወቅቱን የጠበቀና ፈጣን የሆነ ምላሽ መረጃን መስጠት ተገቢ እንደሆነም ገልፀዋል።

ይህም ቤተሰብ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ እምነት አሳድሮ ልጆቹን እንዲልክ ያስችለዋል ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው “የ2011 ዓመት በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ያሉ ተጋላጭነትን በምን መልኩ እንዝጋና የባለድርሻ ሚና” በሚል ባቀረቡት የመወያያ ርዕስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለብጥብጥ የሚዳርጉ ትናንሽ የሚመስሉ ጥያቄዎች ላይ መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።

በተለይ ተቋማቱ የጥበቃ፣ የክሊኒክ፣ የምግብ ቤት፣ የመኝታ ቤት አገልግሎትን እንደዚሁም  የሬጅስትራር፣ የኮሌጅ አስተዳደርና የመዝናኛ ቤት ላይ ለሚነሱ ችግሮች ጥንቃቄ የተሞላበት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ተማሪዎች ስለ አገራቸው ነባራዊ ሁኔታ እንዲያውቁና እርስ በርስ እንዲተዋወቁ የመኝታ ቤት ምደባ አገራዊ መልክ ይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይ በተቋማቱ የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ በስነ ምግባር ጉድለት የሚባረሩ ተማሪዎች ሌላውን እንዳያውኩ፣ የውኃና የመብራት መቆራረጥ ችግር ለመቅረፍ ሁሉም ተቋማት አስቀድመው ዝግጅት እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ባለፈው ዓመት በመማር ማስተማር ሂደት የታዩት ችግሮች እንዲቀረፉ መንግስት የህግ የበላይነትና ሰላም ላይ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ተጠባበቂ ፕሬዝዳንት አቶ ኤሊያስ ዑመር እንዳሉት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሚከሰቱ ችግሮች ተማሪዎች የመፍትሄ አካል አድርጎ መንቀሳቀስ ተገቢ ነው።

የወለጋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኤባ ሚጀና በበኩላቸው ጥቂት ተደራጅተው የውሸት ድረ-ገጽ ከፍተው የዩኒቨርስቲውን ገጽታ ለማበላሸት በሚንቀሳቀሱት ላይ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባት አባ ኤርሚያስ እንዳሉት በተማሪዎች አቀባበል ላይ የፍቅርና የአክብሮት አቀባበል በማድረግ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።

ሼህ አቡዱቃድር የተባሉ የሀይማኖት አባት በበኩላቸው በብሔር የሚለያዩትን ትተን ተማሪዎች ወደ ተሳሳተ አካሄድ እንዳይሄዱ ከመንግስት ጋር ሆነን ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል ብለዋል።

አባ ገዳ ቃበቶ ኤደሞ በሰጡት አስተያየት ደግሞ ኢትዮጵያዊያን በሌሎች አገራት መብታቸው ተከብሮ በሚሰሩበትና በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ተማሪዎች በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሰው እንዲማሩ ማድረግ ይኖርብናል ሲሉ ነው ያሳሰቡት።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙባቸው አካባቢዎች ያሉ ማህበረሰብ ከትምህርት ተቋማቱ ጋር በጋራ ተማሪዎች ተረጋግተው እንዲማሩና ቤተሰቦቻቸውም አምነው ልጆቻቸውን እንዲልኩ የሚያስችል ተግባር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ ከሁሉም ክልሎች የተወከሉ የሐይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችና ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

መንግስት ብቁ ዜጋ ለመፍጠር ለሰው ኃይል ልማት ከአጠቃላየ ዓመታዊ በጀቱ እስከ 25 በመቶ የሚሆን መድቦ እየሰራ ነው ተብሏል። (ኢዜአ)