ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶችና ህጻናት የምክር አገልግሎትና የህግ ድጋፍ በነፃ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን የሕግ ባለሙያዎች ተናገሩ

በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች እና ህጻናት የምክር አገልግሎት እና የህግ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ በበጎ ፈቃደኝነት የነጻ አገልግሎት  ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን የሕግ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበር አባላት እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች በጋራ በመሆን በአዲስ አበባ ከተማ  የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ስር ባሉ መዋቅሮች የህግ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች በበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች እና ህጻናት  ከሕግ ድጋፍና ከምክር አገልግሎት ጀምሮ ጥብቅና እስከመቆም ድረስ ነጻ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም ነው ያስታወቁት፡፡

የአዲስ አበባ የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሜሮን አራጋው በበኩላቸው የማህበራቱ አባላት ያደረጉት የበጎ ፍቃድ ተግባር በከተማዋ ጥቃት ደርሶባቸው በገንዘብ ችግር ምክንያት የሕግ ከለላ ያላገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በባለፉት ዓመታት ቢሮው እና ፖሊስ እንዲሁም ከፍትህ አካላት ጋር በመተባበር በከተማዋ  የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ 13 ሺህ 500 ሴቶች እና ህጻናት የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት መሰጠቱን ምክትል ሃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ከማህበራቱ አባላት እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ጋር በመቀናጀት በሴቶች እና ህጻናት ላይ ጥቃት የሚያደርሱ አካላትን በአፋጣኝ ለህግ ለማቅረብ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ (ምንጭ፤አዲስ አበባ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ)