የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዓመታዊ የቅዲስ ሲኖዶስ ጉባኤ ማካሄድ ጀመረች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዓመታዊ የቅዲስ ሲኖዶስ ጉባኤ ማካሄድ ጀምራለች፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በይፋ ሲጀምር ያለፈው አመት  በሲዶስ መካከል የነበረው መከፋፈል አብቅቶ ሃዋሪያዊ ስራ የተሳካ አንዲሆን የተደረገበትና በዛው ልክ ፈተናዎችም የበዙበት መሆኑ ተነስቷል፡፡

ከቅርብ አመታት ወዲህ ቤተክርስቲያኗ እየገጠማት የመጣውን የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሀብት አያያዝ፣ የምእመናን ፍልሰትና ተያያዝ ነጥቦች ጉባኤው እንደሚመክርበት ተገልጿል፡፡

አሁን ካለንበት ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ጋርም በዜጎች መካከል ፍትና ርትዕ አንዲሰፍን ቤተክርስቲያን ሚናዋን በምትወጣበት አግባብ በስፋት እንደሚመክር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርሲቲያን ፓትሪያርክ ብፅዑ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ተናግረዋል፡፡  

በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ በብሩህ ተስፋ እና ስጋት መንታ መንገድ ላይ የምትገኝ ሲሆን ስጋቱ ተወግዶ ብሩህ ተስፋ እንዲፈነጥቅ አባቶች ህዝቡን የማስተማር ኃላፊነት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።  

የቤተክርስትያኗ መምህራንና ምዕመናን ለህዝብ ወንድማማችነት፣ እኩልነት፣ ለሀገር ወዳድነትና ለዜጎች ደህንነት በጋራ የሚሰሩበት ወቅት መሆኑንም ነው ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ያስገነዘቡት።  

የቤተክርቲያንን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል መሪ እቅድ ዙሪያም ውይይት እንደሚደረግበት ጠቁሟል፡፡

በታሪክ አጋጣሚ ተለያይተው በቆዩት ኤርትራና ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናት በጋራ መስራት የሚያስችል ኮሚሽን በሚቋቋምበት ሁኔታ ጉባኤው መክሮ ውሳኔ አንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል ሲሉ ፓትሪያርኩ ጠቁመዋል፡፡

የሲኖዶሱ ጉባኤ በተጠቀሱ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት መክሮ ሀገራችንና ቤተ ክርስቲኗን የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ ላይ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስን ጨምሮ ከሁሉም አህጉረ ስብከትና በውጭ ሀገራት የሚገኙ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት ተሳታፊዎች ናቸው ተብሏል።