በበጀት ዓመቱ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ 106 ሺህ ነዋሪዎችን በልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል -ኤጀንሲው

በዘንድሮ ዓመት አዲስ አበባ ለማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ እና ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ 106 ሺህ ነዋሪዎችን በሴፍቲኔት መርሃ ግብር ተጠቃሚ ለማድረግ ማቀዱን  በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማህበራዊ ጥበቃና ልማታዊ ሴፍቲኔት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡    

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሁነኛው አየለ እንደገለጹት 106 ሺህ ነዋሪዎችን በልማታዊ ሴፍቲኔትና በኑሮ ማሻሻያ የሥራ ቅጥር ተጠቃሚ ለማድረግ  ታቅዶ እየተሠራ  መሆኑን አስታውቀዋል ። 

 በ2011 በጀት ዓመት መሪ እቅድ ውይይት ላይ  የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድና ልማታዊ ሴፍቲኔት ተግባራትን በማጠናከር ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ነዋሪዎችን በልማታዊ ሴፍቲኔት እና በኑሮ ማሻሻያ የስራ ቅጥር አማካኝነት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን  ዳይሬክተሩ ገልጸዋል ፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ በ116 ወረዳዎችም ለማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ነዋሪዎችን በማህበራዊ ጥበቃ ፈንድ እና በልማታዊ ሴፍቲኔት የቀጥታ ድጋፍ መርሐ ግብር በአጠቃላይ 106 ሺህ ነዋሪዎች  እንደሚካተቱ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ለማህበራዊ ጥበቃና ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብሩ በከተማ አስተዳደሩና በበጎ ፈቃድ  ወጣቶች እንዲሁም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች 50 ሚሊየን ብር፣ ከዓለም ባንክ ደግሞ 133 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተገኝተው በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕፃናትን፣ ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ አቅመ ደካማ አረጋውያንን እና የቀጥታ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በመለየት ተጠቃሚ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሁናቸው ተናግረዋል፡፡

የማህበራዊ ጥበቃና ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር በመንግስት፣ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ፣ በበጎ ፈቃድ ወጣቶች እና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የቁሳቁስ ድጋፍ በ2009 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በዚህም ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማግኘታቸው ተገልጸዋል፡፡ (ምንጭ፤የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ)