በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን ዝግጅት ተደርጓል – ዶ/ር ደብረፅዮን

በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል አስታወቁ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች መማር ማስተማሩን ሰለማዊ ለማድረግ የተደረገውን ዝግጅት በተመለከተ በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ትምህርት የእውቀት፣ ቴክኖሎጂ፣ ሳይንስ እንዲሁም የሀገሪቱ ኢኮኖሚና ፓለቲካ መሪዎች የሚፈልቁበት በመሆኑ  የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊና የተረጋጋ እንዲሆን ይጠበቃል ብለዋል በመግለጫቸው።

የተረጋጋ ሁኔታ ከሌለ ተማሪዎች በአግባቡ መማር እንደማይችሉ የገለፁት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ፥ ለዚህም በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩንቨርስቲዎችና በክልሉ መንግስት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ከዚህ በፊት ባሉት ዓመታት በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የመማር ማስተማሩን የሚያውኩ ሁኔታዎች ብዙም አለመስተዋላቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም ችግሮች አይከሰቱም ተብሎ ስለማይታለፍ እንደ መንግስት ተቋማቱ ሰላማዊ እንዲሆኑ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎል ሲሉ አስታውቀዋል።

ተማሪዎችም ችግሮች ካሉ ተወያይተውና ተነጋግረው  እንደሚፈቱ እምነቴ ነው በማለት  ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።

በዘንድሮው ዓመት በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ችግር እንዳይፈጠር ምክክር መደረጉንና ነባርም ሆኑ አዲስ ዩኒቨርስቲዎች ችግሮችን በመካከር መፍታት እንዳለባቸውና ለዚህም መንግስት ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል።

የክልሉ ህዝብ  ዘርና ቋንቋ ሳይለይ ሁሉንም አክባሪ መሆኑን የገለፁት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ህብረተሰቡ በትምህርት ተቋማት ያሉ ተማሪዎችን አክብሮና ደግፎ ያቆያል ብለዋል።

ተማሪዎችም ችግሮች ካሉ በአግባቡ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ እንዳለባቸው ያሳሰቡ ሲሆን፥ የሚነሱትን ችግሮች ወደ ብሄርና እምነት በመውሰድ ችግር መፍጠር  እንደማያስፈልግም አስታውቀዋል።

ከየትኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ልጆቻቸውን በክልሉ ወደሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሚልኩ ወላጆች  ስጋት ሊፈጠርባቸው እንደማይገባና ወደ ቤተሰቦቻቸው እንደላኳቸው አድርገው እንዲወስዱም ጠይቀዋል።

በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች ውጤታ መሆን እንዲችሉ የክልሉ መንግስት ፍላጎት መሆኑንና ለዚህም ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)