በማረሚያ ተቋማት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ላይ የሚመክር መድረክ በአዲስ አበባ ተጀመረ

በማረሚያ ተቋማት የሰብዓዊ መብት አያያዝን በሚመለከት ስድስት የአፍሪካ ሃገራትን ያሳተፈ  የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡

ዛሬ በተጀመረው የምክክር መድረክ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ጋና እና ናይጄሪያ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

በዚህ መድረክ ልምድ ከመለዋወጥ ባሻገር የማረሚያ ቤቶች ግንባታ ደረጃ፣ የታራሚዎች  የምግብ አቅርቦትና የጤና ሽፋን ምን መምሰል እንደሚኖርበት እና መሰል ጉዳዮች ላይ  ሰፊ ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል፡፡

የፌዴራል የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ከአለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ/ICRC/ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ መድረክ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከሰላሳ የሚበልጡ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የስራ ሃላፊዎች፤  ከስድስቱ ሃገራት እና ከ ICRC የተውጣጡ አካላት እየተሳተፉበት ነው፡፡

ኢትዮጵያም ከመድረኩ ሰፊ ልምድ በማግኘት የጀመረቻቸውን የለውጥ እንቅስቃሴዎች በዘርፉ እንደምትጠቀምበት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳዳሪ አቶ ጀማ አባሶ ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ጀማል ገለጻ ሃገሪቱ የጀመረቻቸውን ዘርፈ ብዙ የለውጥ ስራዎች በማረሚያ ቤቶች የታራሚዎችን የሰብዓዊ መብት በማሻሻል ለማስቀጠል ሰፋፊ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡

በሚቀጥለው ሀሙስ መቋጫውን የሚያገኘው ይህ የምክክር መድረክ ሃገራቱ ፈተናዎችን በመለየት የተሻለ የህግ ታራሚዎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ አዎንታዊ ተሞክሮ የሚያገኙበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡