በህገወጥ ግንባታዎችና ማስፋፊያዎች ምክንያት የመግቢያና መውጫ መንገድ ተዘግቶብናል– በማህበር ተደራጅተው ቤት የገነቡ ነዋሪዎች

አካባቢያቸው በህገ-ወጥ ግንባታዎችና ማስፋፊያዎች ምክንያት የመግቢያ መውጫ መንገድና የፍሳሽ ማስወገጃ ቦታ ተዘግቶብናል ሲሉ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 በማህበር ተደራጅተው ቤት የገነቡ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

ለአካባቢው መሰረተ ልማት የሚወሉ ቦታዎችን በህገ ወጥ መልክ ግንባታ በማካሄድ ለችግር እየተዳረግን ነው ያሉት ነዋሪዎቹ ችግሩን በተደጋጋሚ ብናመለክትም መፍትሄ የሚሰጠን አካል አጥተናል ብለዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ቀደም ሲል ለነበሩት አመራሮች በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ብናቀርብም ቀጠሮ እየሰጡ ማጓጓተታቸውን ተናግረዋል፡፡

ቅሬታቸውን በማስመልከት ዋልታ ያነጋገረው በክፍለ ከተማው አዲስ የተመደቡት የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገለታው ዘዬዴ በአካባቢው ላይ በቅርቡ በተደረገው ማጣራት አላግባብ ማስፋፋትና ግንባታ ማካሄድ የመሳሰሉ ህገ ወጥነት ሰፍኖ መቆየቱ እንደተረጋገጠ ገልጸዋል፡፡

በዚሁም ማጣራት በተደረጉና በአካባቢው ከተሰሩ ሰባት ግንባታዎች አንዱ ብቻ በትክክለኛው ካርታ መሠረት መገንባቱን የገለጹት ኃላፊው ሌሎች ስድስት የሚሆኑት በህገወጥ ማስፋፊያ ከ28 እስከ 120 ካሬሜትር በላይ መመሪያውን በመጣስ በህገወጥ መልክ ማስፋፋታቸውንና የአንዱ ግንባታ ሙሉ በሙሉ የአየር ካርታ የሌለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በህገ ወጥ ተግባር የተሳተፉ ግለሰቦች የመሬት ካርታው እንዲመክን እንደሚደረግና የተወሰደው መሬትም ለመሬት ባንክ ገቢ እንዲደረግ ውሳኔው መተላለፉን ኃላፊው ገልጸው በዚህ ተግባር የተሳተፉ አመራር አካላት ላይ ማጣራት ተደርጎ በቀጣይ ተጠያቂ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡

በቀጣይም በእነዚህ ህገ ወጦች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድና ነዋሪዎቹ የሚያነሱት ችግርም በቅርቡ እንደሚፈታ ነው የተናገሩት፡፡