ወባን ለመከላከል በሚደረገው የኬሚካል ርጭት ጥራት ላይ ውይይት እየተደረገ ነው

ወባን ለመከላከል በየቤቱ በሚደረገው የኬሚካል ርጭት ጥራትና ውጤታማነት ላይ ውይይት እየተደረገ ነው፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ወባን ጨርሶ ለማስወገድ የሚያግዘውንና በየቤቱ የሚደረገውን የኬሚካል ርጭት ጥራትና ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ግምገማዊ ውይይት በአዳማ ተጀመሯል።

በዋናነት ርጭቱን በተመለከተ በ2010 ዓ.ም አፈፃፀምና በ2011 ዓ.ም ረቂቅ ዕቅዶች ላይ በማለም የሚከናወነው ይሄው ግምገማዊ ውይይት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከል ዳይሬክቶሬት የወባ መከላከልና ማጥፋት ኬዝ ቲም አማካኝነት የተዘጋጀ ነው።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው የግምገማ መድረክ ላይ በአሰራሩ ዙሪያ ከአገራዊ ሪፖርት በተጨማሪ የዘጠኙ ክልሎችና የድሬደዋ አስተዳደር ተወካዮች የአፈፃፀምና የዕቅድ ሪፖርታቸውን አቅርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

በየዓመቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የበሽታው ስርጭት በሚያሰጋባቸው አካባቢዎች ለሚከናወነው የርጭት ፕሮግራም እስከ አንድ ቢሊዮን ብር የመንግስት በጀት ወጪ እንደሚሆን የገለፁት በሚኒስቴሩ የበሽታዎች መከላከል ዳይሬክቶሬት የወባ መከላከልና ማጥፋት ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ መብራሃቶም ኃይለ ናቸው፡፡

ይህን ከፍተኛ በጀት በአግባቡና በጥራት ጥቅም ላይ ለማዋል የግምገማ መድረኩ መልካም አጋጣሚ ነውም ብለዋል።

የወባ ስርጭቱ በመላ አገሪቱ መቀነሱ እየታወቀ አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ዒላማቸውን ያልጠበቁ የርጭት መርኃ ግብሮች እንደሚከናወኑ የተገለፀ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች በስልጠና ያልታገዘ አሰራርን የመከተልና ከልማዳዊ አሰራር አለመውጣት፣ የግብዓቶች እና የበጀት እጥረት መኖሩ፣ ለርጭት ባለሙያዎች የሚከፈለው አበል ወቅቱን ያላገናዘበና ከቦታ ቦታ የተለያየ መሆን እና ሌሎችም የአስራር ክፍተቶች እንዳሉ በሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በኢትዮጵያ ወባን ለመከላከል የሚደረገው የቤት ለቤት የኬሚካል ርጭት በ1958 ዓ.ም የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ ከ150 ሺ በላይ ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈበት ጊዜ ጀምሮ መከናወን የጀመረ መሆኑና በአግባቡ ከተከወነ ውጤታማ የመከላከያ መንገድ መሆኑ በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል።/መረጃው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነው/